Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ውጤታማ ተሞክሮዋን የምታካፍልበት የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባዔ…

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ አየር ንብረትና በአፍሪካ ካሪቢያን ጉባዔዎች ብሔራዊና አህጉራዊ ጥቅሞችን የሚያስጠበቁ አጀንዳዎችን በማቅረብ መሪ ሚናዋን ትወጣለች አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ÷ የአፍሪካ ካሪቢያን ማህበረሰብ እና ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔዎች በስኬት ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አፍሪካ በብራዚል በሚካሄደው 30ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ የራሷን ድምፅ ይዛ የምትቀርብበትን ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ በሚከናወነው ጉባዔ ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች እንደሚሳተፉ ጠቁመው÷ አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጋራ የሆነ አፍሪካዊ ስልት የሚቀይሱበት መድረክ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው ሀገራዊና አህጉራዊ አጀንዳን በማቅረብ መሪ ተዋናይ እንደምትሆንና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የመከላከል ውጤታማ ተሞክሮዋን እንደምታካፍል አንስተዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ካሪቢያን ማህበረሰብ ጉባዔ “ለአፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን የማካካሻ ፍትህን ለመሻት አህጉር ተሻጋሪ አጋርነት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን÷ የጋራ ድምፅ ማሰማት እንዲችሉ መሰረት እንደሚሆን ገልጸዋል።

ጉባዔው የአፍሪካና ካሪቢያን ሀገራት በደቡብ ደቡብ የትብብር መንፈስ ግንኙነታቸውን ለማጎልበት፣ አፍሪካ ከካረቢያን ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና ትብብር ለማሳደግ ያስችላታል ነው ያሉት፡፡

ጉባዔው በዓለም የፋይናንስ ስርዓት፣ በቱሪዝም፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ እንደሚመክር ያነሱት ቃል አቀባዩ÷ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የካሪቢያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዲሰማሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያበስር ትልቅ ፕሮጀክት ነው፤ ኢትዮጵያ ለቅኝ ግዛት እሳቤዎች ቦታ የላትም፤ በጋራ ተጠቃሚነትና ልማት ላይ የተመሰረተ ፅኑ ፍላጎት አላት ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

Exit mobile version