አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሒደት አታካችና አድካሚ ቢሆንም ፍሬው እጅግ ጣፋጭ ሆኗል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የጉባ ላይ ወግ” በተሰኘ ልዩ ቃለ ምልልስ ላይ ባደረጉት ቆይታ ፥ የግድቡ ግንባታ ሒደት አድካሚ፣ አታካች፣ አጨቃጫቂና ከዓላማ የሚያዛባ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢ ፍትሃዊ በሆነ ዓለም ውስጥ ፍትሕን በመጠበቅ በእጅጉ መፈተኑን እና በምሬት የተሞላ ጊዜ ማሳለፉን አንስተዋል፡፡
በግድቡ ምክንያት የወንዙ ውሃ ካልተቋረጠና ሌላውን የማይጎዳ ከሆነ ኢትዮጵያ ኃይል ማመንጨቷ እንደ ችግር ተቆጥሮ ጫና መብዛቱ እንድንትክዝ የሚያደርግ ጉዳይ ሆኖ መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡
የጸጥታውን ምክር ቤት ጨምሮ የተለያዩ አካላት በግድቡ ጉዳይ መምከራቸውን አስታውሰው ፥ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት እንድታቆም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችና ማስፈራሪያዎችን አስተናግዳለች ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አክለውም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት በየዕለት ተዕለት ሥራዎቻችን ላይ ጫና ሲደረግብን ነበር ብለዋል፡፡
የዓለም ተቋማት እንደ ሕዳሴ ግድብ ላሉ ሥራዎች ብድር እና እርዳታን እንደማይሰጡ ጠቅሰው፥ በዚህም ከፍላጎታቸው ጋር የሚጣጣም ሃብት የሌላቸው ሀገራት በሃብት ውስንነት ምክንያት ይታሰራሉ ነው ያሉት፡፡
አባይ ሳንጠቀምበት መፍሰሱንና አፈራችንን እየወሰደ ነው የሚሉ ቁጭቶችን በሥነ ቃሎቻችንና በግጥሞቻችን ሲነገሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፥ ነገር ግን ዓባይ ከውሃ፣ ከአፈርና ከአሳዎቻችንም ባለፈ ወርቃችንን ይዞ ሲሄድ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በግድቡ አማካኝነት በውሃ ተጠራርጎ ሲሄድ የነበረውን ደለል ስናስፈትሽ ወርቅ እያገኘንበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ ዓባይ ወርቃችንንም ይዞ ሲሄድ ነበር የሚል ተጨማሪ ቁጭት መፈጠሩን አንስተዋል፡፡
ሃብታችንን ሲጠቀሙ የኖሩ ሀገራት በምላሹ ኢትዮጵያን ከማመስገን ይልቅ ሀብቷን ልጠቀም በማለቷ ቁጣ እና ተግሳጽ እየሰማን ነው ብለዋል፡፡
በግድቡ ምክንያት የተቋረጠ ውሃ እንደሌለ ገልጸው ፥ እንደከዚህ ቀደሙ ድፍርስ ሳይሆን የጠራ ውሃ ወደ ተፋሰሱ ሀገራት እየሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በግድቡ ግንባታ ሒደት ያለፍንበት መንገድ ምን ያህል ከባድ እና ፈታኝ መሆኑ የሚታወቀው በግድቡ ምክንያት ካጣናቸው ጉዳዮች ጋር አገናኝተን ስንመለከተው ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ግድቡ በመገንባታችን የዓባይን ውሃ ቁጭትና ሃዘን ከማስቀረት ባለፈ ለእኛም ለአካባቢውም ብስራት የሚሆን ብርሃን አውጥተናል ነው ያሉት፡፡
ግድቡ ወርቅ እና አፈራችንን እንዳናጣ ከማድረጉ በተጨማሪ ለብዙ ጨለማ ለወረሳቸው ሕዝቦች ብርሃንን መፈንጠቅ ችሏል ያሉ ሲሆን ፥ ይህ ለእኛም ሆነ ለከባቢው ትልቅ ብስራት መሆኑን አውስተዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ሒደት አድካሚ፣ አታካች፣ አጨቃጫቂና ከዓላማ የሚያዛባ እንደነበር አስታውሰው ፥ ፍሬው ግን እጅግ ጣፋጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ