Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ታሪክ የምንሻማ ሳንሆን ታሪክ የምንሰራ ትውልድ መሆናችንን መገንዘብ ያስፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ታሪክ የምንሻማ ሳንሆን ታሪክ የምንሰራ ትውልድ መሆናችንን መገንዘብ ያስፈልጋል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የጉባ ላይ ወግ” በተሰኘ ልዩ ቃለ ምልልስ ላይ ባደረጉት ቆይታ፥ አባቶቻችን በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት አልመዋል፣ ተግተዋል፤ ብዙ የኪነ ጥበብ ሥራዎችም በጉዳዩ ላይ ተሰንደዋል ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

ያምሆኖ ግን የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ2003 ወቅቱ በሁሉም ዘርፍ ምቹ መሆኑን ተገንዝበው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማስጀመራቸው ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ይሄም ከአንድ ሀገር መሪ የሚጠበቅ ተግባር ተደርጎ መገለጽ እንዳለበት ጠቅሰው÷ ይሁን እንጂ እሳቸው ግድቡ በተጀመረ በዓመቱ በማለፋቸው በወቅቱ የግንባታ ዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ግድቡን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ እየተንገዳገደ የተወሰነ ቦታ እንዲደርስ ስለማድረጋቸው ማመስገን ይገባል ብለዋል፡፡

በወቅቱ የፕሮጀክት አስተዳደር ውስንነት እንደነበር አንስተው÷ ይህም የኢትዮጵያ አጠቃላይ ፖለቲካ የነበረበት ሁኔታ ያሳደረው ተጽዕኖ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በፊት የነበረው ሥራ አሁን ካለው አጨራረስ ጋር ሊወዳደር አይችልም፤ በግድቡ ሳቢያ ግጭትና ሳቢያ የበዛው በአጨራረሱ ሥራ ወቅት እንደነበር አብራርተዋል፡፡

በግድቡ ዙሪያ የእኛም ዘመን ሆነ ከዚያ በፊት የነበረው ዘመን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሚና አይተካውም፤ ዋናው የጉዳዩ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ነገር ግን በየዘመኑ ጉዳዩን ወስነው የመሩ ሰዎች በልካቸው ሳይጋነንም፤ ሳያንስም ተገቢ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ እኛ ታሪክ የምንሻማ ሳንሆን ታሪክ የምንሰራ ትውልድ መሆናችንን ማሰብ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) 2018 የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ይሆናል ብለው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ዓመቱ የማንሰራራት መሆኑን ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ዓለም ከዓባይ ጋር የሚመሰክረው እና የሚያየው ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲክስ ከመቀየሩ ባለፈ ዓባይ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕልሞች ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

በእኔ ምኞት ከሚቀጥለው ሳምንት ወይም 15 ቀናት በኋላ የሕዳሴ ግድብ ለመላ ኢትዮጵያውያን ለጉብኝት ክፍት ይሆናል ብለዋል፡፡

ለጎብኝዎች የአውሮፕላን ማረፊያና ከ100 በላይ ቪላዎች መዘጋጀታቸው ጠቁመው÷ በዚህም ለዘመናት ቀፍድዶ የያዘንን ችግርና ትልቁን ፈተና የአሁኑ ትውልድ እንዴት ሰብሮ እንዳስቀረው ማየትና መማር አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ለሳሊኒ ኩባንያ፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሠራተኞች፣ ለጋዜጠኞች፣ አርቲስቶች፣ ምሁራን፣ ዳያስፖራዎች፣ ለመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች ጸጥታ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ጀምሮ የመጨረሽ፣ ጨርሶ ደግሞ ፍሬውን የወል የማድረግ ልምምዳችን እያደገ ከሄደ ለእኛም፤ ለመላው አፍሪካም በብዙ ትምህርት የሚሰጥ ሥራ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version