Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በባህርዛፍ የተያዘ መሬትን ወደ ፍራፍሬ ልማት የመቀየር ውጤታማ ተሞክሮ …

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በባህርዛፍ የተያዙ ለም መሬቶችን ወደ ፍራፍሬ ልማት በመቀየር አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንዳሉት÷ በክልሉ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር በተለያዩ ዘርፎች ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡

በዚህም በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብሎም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለሚደረገው ጉዞ መሰረት የሚጥል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ለአብነትም በክልሉ በተጀመረው 30-40-30 የፍራፍሬ ልማት ኢኒሼቲቭ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ነው ያስረዱት፡፡

በኢኒሼቲቩም የመሬት አጠቃቀምን ለማሻሻልና ምርታማነትን ለማሳደግ መንገድ ዳር የሚገኙና በባህር ዛፍ የተያዙ ለም መሬቶችን ወደ ፍራፍሬ ልማት የመቀየር ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ባህርዛፍ በተፈጥሮው የመሬት ለምነትን ከመቀነሱ ባለፈ ለአርሶ አደሮች የሚሰጠው ጥቅም ውስን እንደሆነ በጥናት ተለይቷል ነው ያሉት።

ይህን ተከትሎም በስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ እና ሌሎች አካባቢዎች በባህርዛፍ ተይዞ የነበረን ለም መሬት ከፍተኛ ጠቀሜታ ባላቸው የፍራፍሬና አትክልት በመተካት ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።

እስካሁን ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሙዝ፣ ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ቡና እና ቅመማ ቅመም መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡

በተሰራው ሥራ የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን ጠቁመው÷ ተሞክሮው በአረዓያነት የሚወሰድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አርሶ አደሮች በፍራፍሬ ልማት በስፋት እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ኡስማን ሱሩር÷ ‎በባህርዛፍ የተያዘ ለም መሬትን ወደ ፍራፍሬ ልማት የመቀየሩ ሒደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version