አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2017 (ኤፍ ኤምሲ) ኢትዮጵያ ተነሥታለች፤ ከእንግዲህ ወደኋላ አትመለስም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሠራራት’ በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ያለውን ጳጉሜን 4 የማንሠራራት ቀንን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ተነሥታለች፡፡ ከእንግዲህ ወደኋላ አትመለስም ብለዋል።
ይሄ የማንሠራራት ጉዞዋ በዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የታገዘ መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡
በተለይም በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በአምራችነት እና በአይሲቲ ዘርፎች የላቁ ውጤቶችን እያስመዘገብን መቀጠል አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዕድገታችን አጋዥ የሚሆን ሀብት መፍጠር እና ገቢ መሰብሰብ ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዕድገታችን የሚያመነጨውን ገቢና ሀብትም በሚገባ ሰብስበንና ቆጥበን ለብልጽግና ግባችን መጠቀም አለብን ብለዋል።
የጀመርነውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በማሣለጥና በማሳካት የኢትዮጵያ ማንሠራራት ወደ ዘላቂ የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲለወጥ እናደርጋለን ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡