Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ወንድሞችን ሐቅ መቼም አታስቀርም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያ ግድቡን የገነባቸው ለመበልጸግና ለቀጣናው ብርሃን እንጂ በፍጹም ጎረቤት ወንድሞችን ለመጉዳት አይደለም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ዳግማዊ ዓድዋ የሆነውና ኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊነት መገለጫ ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ የምረቃ ሥነ ሥርዓት በጉባ እየተካሄደ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ታሪክ ሰምተናል ታሪክ አይተናል፣ ታሪክ ተምረናል፣ ዛሬ ፈጣሪ የመረጠው ትውልድ ስለሆንን ታሪክ ሰርተናል ሲሉ አውስተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ከዚህች ዕለት ጀምሮ ዳግም ዓድዋ በጉባ ላይ በዚህ ትውልድ በመሰራቱ የኢትዮጵያ የልመና፣ ስንፍና እና የእንጉርጉሮ ዘመን አብቅቷል ብለዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ እንደልኳ በመጠኗ የምትለካበት ዘመን ከፊት መምጣቱን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፤ ከተረጂነት ወጥታም ረጂ ትሆናለች ነው ያሉት ፡፡

በዚህ የኢትዮጵያ የማንሰራራት የመጀመሪያ ቀን ከእኛ ጋር ለተገኛችሁ ወዳጆቻችን በእናንተ ዘመን ብቻ ሳይሆን በልጆቻችሁ ዘመን ሁሉ ሀገራችን ወዳጅ ብቻ ሳትሆን ከሁሉም ሃብቷ እንደምታቋድሳቸው አረጋግጣለሁ ብለዋል፡፡

የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያ ግድቡን የገነባቸው ለመበልጸግና ለቀጣናው ብርሃን እንጂ በፍጹምን ጎረቤት ወንድሞቻችን ለመጉዳት እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡

በቅን ልቦና ስጋት የሚያድርባችው ወንድሞቻችንም ኢትዮጵያ የጎረቤቶቻችን ሐቅ መቼም ቢሆን የማታስቀር መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡

የግብጽ ረሃብ፣ የሱዳን ረሃብ እና የሌሎች ወንድሞቻችን ችግር የእኛም ስለሆነ ከወንድሞቻችን ጋር አብረን ከመብላት እና ከመካፈል ውጪ ማንንም የመጉዳት ፍላጎት የለንም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡

ስለሆነም ያለፈውን በመተው በቀጣይ ለሚሰሩ ታላቅ ሥራዎች በጋር እና በትብብር ለመስራት ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version