Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ2018 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አዲሱ አመት የኢትዮጵያን ማንሠራራት የበለጠ ሥር እና መሠረት የምናስይዝበት ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ኢትዮጵያ ማንሠራራት በጀመረችበት እና ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተመረቀበት ጊዜ ለሚከበረው አዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ

ያለፈው ዓመት ፈጣሪ ከጎናችን፣ ስኬት በደጃችን መሆኑን ያየንበት ዓመት ነበር፡፡ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በአምራችነት እና በአይሲቲ ዘርፎች ያስመዘገብናቸው ውጤቶች ይሄንን ይመሰክራሉ፡፡

ኢትዮጵያን ያህል ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንን ያህል ሕዝብ ይዘን በትጋት ከሠራን፣ ከዚህ በላይ ድል ልናሳካ እንደምንችል ምስክራችን የሕዳሴ ግድብ ነው፡፡

ከእርግዝና ወራት ሁሉ እጅግ አስቸጋሪዎቹ፣ እጅግ አስፈሪዎቹ እና እጅግ ፈታኞቹ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት ናቸው ይባላል፡፡ በሕዝብ ልብ ውስጥ ለዘመናት የተጸነሰውን የሕዳሴውን ግድብ ኢትዮጵያ እንድትወልደው ብዙ ፈተናዎችን መሻገር ግድ ነበር፡፡ ብዙ አስቸጋሪ ጊዜያትን ማለፍ ይገባ ነበር፡፡ አያሌ አስፈሪ ተግዳሮቶችን መቋቋም ወሳኝ ነበር፡፡

በተለይም የመጨረሻዎቹ ጊዜያት ወገብን አሥሮ፣ ሐሞትን አምርሮ፣ ወኔን ቋጥሮ፣ ወጥመድን ሰብሮ፣ ሞትን ተሻግሮ መሄድ የሚያስፈልግባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ከፈጣሪ ጋር፣ በሕዝባችን ጽናት፣ በፕሮጀክት ሠራተኞቻችን ብርታት፣ በጸጥታ አባሎቻችን መሥዋዕትነት ያን ሁሉ አልፈን ለምርቃቱ በቅተናል፡፡

የምናከብረው የዓመትን መለወጥ ብቻ አይደለም፡፡ የታሪክን መለወጥ ጭምር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገጽታ፣ የኢትዮጵያ ትርክት፣ የኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካዊ ቁመና ተቀይሯል፡፡ ቀደምቶቻችን ሲመኙት፣ አያቶቻችን ሲያስሱት፣ አባቶቻችን ሲጠብቁት፣ እኛ ስንታገልለት የነበረው የኢትዮጵያ ማንሠራራት እውን ሆኗል፡፡

ይሄ ለሺ ዘመን የከፍታ ጉዟችን መነሻ እንጂ መዳረሻ አይደለም፡፡ ጅማሬ እንጂ ፍጻሜ አይደለም፡፡ እኛ በዐቅምና በአቋም ከተደመርን፣ ሀገራችን ባለ ብዙ ጸጋ ናት፡፡ ለአፍሪካ እና ለዓለም የሚተርፍ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሯዊ ሀብት ሞልቷታል፡፡

2018 የኢትዮጵያን ማንሠራራት የበለጠ ሥር እና መሠረት የምናስይዝበት ዓመት ነው፡፡ በአንድ እጃችን ፈተናዎቻችንን እየተቋቋምን፣ በሌላው እጃችን ታሪካችንን እየቀየርን እንጓዛለን፡፡

ንሥር ከምድር ሲነሣ ብዙ ወፎች እና ነፍሳት አብረውት ሊነሡ ይችላሉ፡፡ ለተወሰነ ጊዜም አብረውት ይበራሉ፡፡ የተወሰነ ሰዓትም ሊሸፍኑት ይደርሳሉ፡፡ የበለጠ ወደ ላይ በመጠቀ ቁጥር ግን ብዙዎቹ ወደታች ይቀራሉ፡፡ በመጨረሻም በሕዋው ላይ የሁሉንም ታሪክ እየተመለከተ ንሥር በድል መጓዙን ይቀጥላል፡፡

እኛም ለኢትዮጵያ ንጋት እና ምጥቀት ያስፈልገናል፡፡ 2018 የኢትዮጵያ ታላቅነት የበለጠ እየነጋ፣ የበለጠ እየበራ፣ የበለጠ እየፈካ የሚሄድበት ነው፡፡ የሕዳሴ ግድብን ባየን ቁጥር የኢትዮጵያን አይበገሬነትና ቻይነት እናስታውሳለን፡፡ ሐይቁን ባየን ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያን ንጋት እናስባለን፡፡ “ንጋት ሐይቅ” የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ግድቡ እስካሁን የነበረውን ይናገራል፡፡ ሐይቁ ከዚህ በኋላ የሚመጣውን ያበሥራል፡፡

ንሥር ከትንሽ ከትልቁ ጋር በሆነ ባልሆነው አይከራከርምም፤ አይነጋገርም፡፡ ወደላይ በመጠቀ ቁጥር ፈተናው እየቀነሰ፣ ዐቅሙ እየጨመረ፣ ታሪኩ እየተቀየረ እንደሚሄድ ያውቀዋል፡፡ ስለዚህም ከግራ ከቀኝ የሚወረወረው እየቻለ ወደ ላይ ይመጥቃል፡፡ እኛም ወደ ላይ ከፍ ባልን ቁጥር ፈተናችን እየቀረ፣ ድላችን እየተጨመረ እንደሚሄድ ዐውቀን፣ አእምሯችንን እና እጆቻችንን ለሥራ ማሰለፍ አለብን፡፡

ኢትዮጵያን የሚቀይራት የልጆቿ ፍጥነትና ፈጠራ ነው፡፡ የዓባይን ታሪክ የቀየረው ሥራ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚቀይረውም ሥራ ነው፡፡

በየቢሮው፣ በየእርሻው፣ በየግንባሩ፣ በየድርጅቱ፣ በየትምህርት ቤቱ፣ በየተቋማቱ ያለን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልባችንን፣ ሐሳባችንን፣ ዕውቀታችንን እና ጉልበታችንን ለኢትዮጵያ ብልጽግና እናውለው፡፡

ስንሠራ ምን እንደምንቀይር ከሕዳሴው ግድብ አይተናል፡፡ እኛ ለስኬት ስንረባረብ ፈጣሪ ምን ያህል እንደሚረዳን እኛው ምስክር ነን፡፡

የሺ ዘመናትን ጥያቄ እንድንመልስ ኃይል የሰጠ ፈጣሪ፣ የዓመታትንና የወራትን ጥያቄ ለመመለስ አይሳነውም፡፡ 2018 ዓመት ይሄንን ይበልጥ የምናረጋግጥበት እንደሚሆን አምናለሁ፡፡

ዛሬ ዓይኞቻችን ያዩትን ለማየት፣ ጆሮዎቻችንም የሰሙትን ለመስማት እንዲችሉ መሥዋዕትነት ለከፈላችሁት ሁሉ እጅ እንነሳለን፡፡

በሁሉም መስክ የተሳተፋችሁትን ሁሉ ኢትዮጵያ ታከብራችኋለች፡፡

ከጎናችን የነበራችሁትን ወዳጅ ሀገሮች እና ሕዝቦች ሁሉ በኢትዮጵያ ስም እናመሰግናችኋለን፡፡ ዕድገትና ብልጽግና የቅብብሎሽ ውጤት ነው፡፡

የጀመራችሁ፣ ያስቀጠላችሁ፣ ለፍጻሜ የታገላችሁ ስማችሁን በሕዳሴ ግድቡ ላይ ጽፋችኋል፡፡ በገንዘብ፣ በዕውቀት፣ በጉልበት፣ በሚዲያ፣ በዲፕሎማሲ፣ በሞያ፣ ወዘተ. የምትችሉትን ያበረከታችሁ ሁሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ሆናችሁ በታሪክ ሠፍራችኋል፡፡

ይህ ተጋድሏችን፤ ይህ ትብብራችን፤ ይህ ለብሔራዊ ጥቅም በአንድነት መቆማችን፤ ይህ ለራሳችን፣ በራሳችን፣ ከራሳችን መሥራታችን ነገም መቀጠል አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ይገባታል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህም በላይ ታላላቅ ሥራዎች ይጠብቋታል፡፡ ይሄንንም አብረንና ተባብረን ልናሳካላት ይገባል፡፡

አዲሱ ዓመት የኢትጵያ ማንሠራራት የበለጠ መሠረት የሚይዝበት እንደሚሆን አምናለሁ፡፡

በድጋሚ መልካም አዲስ ዓመት ይሁን
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጳጉሜን 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Exit mobile version