Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና 8 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች አለፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከተፈተኑት 8 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች አልፈዋል አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።

የ2017 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እንዳሉት፤ ዘንድሮ ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከተፈተኑት መካከል 8 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት አልፈዋል።

በዚህም በአጠቃላይ ዘንድሮ 48 ሺህ 929 ተማሪዎች ማለፋቸውን ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት አማካይ ውጤት 29 ነጥብ 7 እንደነበር አስታውሰው÷ ዘንድሮ 31 ነጥብ 67 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል ነው ያሉት።

በዚህም በተፈጥሮ ሳይንስ 11 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ 5 ነጥብ 2 በመቶ በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ 8 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት ማለፋቸውንም አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ሀረሪ እና አማራ ክልል በአማካኝ ከፍተኛ ተማሪዎች ያሳለፉ ሆነው መመዝገባቸውን አመልክተዋል።

በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት መስክ ከፍተኛ ውጤት ከ600፤ 591 ሆኖ እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ ከ600፤ 562 ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል።

እንዲሁም 2 ሺህ 384 ተማሪዎች ከ500 በላይ ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከፈተና ጋር በተያያዘ በመስረቅ እና በኩረጃ እንዲሁም በተገቢው መንገድ ተማሪዎች ፈተና ባለመውሰዳቸው ማን በትክክል ለዩኒቨርሲቲ ብቁ መሆኑን መለየት አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው÷ በዚህ ዓመት ግን 120 ተማሪዎች ብቻ በዚህ መልኩ መያዛቸውን አውስተዋል።

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version