አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ብልፅግና ምኞት ብቻ ሳይሆን እንደሚቻል ያሳየ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት “የመደመር መንግስት” መጽሐፍ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የመደመርን መንግስት የሆልዮሽ ጉዞውን ከዳሰሰ በኋላ መዳረሻውን በግልፅ የሚያስቀምጥ መጽሐፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመደመር መንግሥት ከምኞት እና መሻት የተሻገረና መቼ ምን ብናሳካ የት ልንደርስ እንችላለን የሚሉ እቅዶችን በግልፅ ያመላከተ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብልጽግና ምኞት ሳይሆን እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
የመደመር መንግሥት እቅዶች የማይፈፀሙ በመሻት ብቻ የሚቀሩ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና በሚያረጋግጥ መልኩ በተያዘላቸው ጊዜ የሚፈፀሙ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የመፈፀም ብቃታችንን በብዙ መንገድ አስመስክረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ራዕያችን የምትመስል ሀገር ሳይሆን የምትመሰል ሀገር መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በዓባይ ግድብ እና ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች የተመዘገበው ስኬት የመደመር መንግስትን የማቀድ እና የመፈፀም አቅሙን ለዓለም ያሳዩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
አሁን ላይ በራስ አቅም፣ በራስ ገንዘብ እና ባጠረ ጊዜ እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመው÷ እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን የአፍሪካ ምሳሌ እንደሚያደርጓትም አስገንዝበዋል፡፡