Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የምትችልባቸው ዓለም አቀፍ ህጎች አሉ – የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የምትችልባቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው አማራጮች አሏት አሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በሀገራቸውና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከአል አረቢያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄና የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

የባህር በር በተለይም ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እንዲሁም ለጸጥታና ደህንነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፥ ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት እንዳላት አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምትችልባቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው አማራጮች እንዳሏት ነው ፕሬዚዳንቱ ያስገነዘቡት፡፡

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፥ ግድቡ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለቀጣናው ሀገራት ጉልህ አበርክቶ አለው ብለዋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው የግድቡ ምረቃ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንቱ፥ የግድቡ ዓላማ በዋናነት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መሆኑንም በቃለ ምልልሳቸው ላይ አንስተዋል፡፡

ግድቡ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ለቀጣናው ሀገራት ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ለማንኛውም ልማት መሠረት መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ አንጻር ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አዎንታዊና እንደ አንድ የመንግስት ፕሮጀክት ስኬታማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሀገራቸው በግድቡ ዙሪያ በተለይም በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል አዎንታዊ መፍትሄ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ አና ሶማሊያ ሰፊ ድንበር የሚጋሩ ሀገራት መሆናቸውን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ በሶማሊያ ሰላም ማስከበር የምታደርገውን ተሳትፎ አውስተዋል፡፡

Exit mobile version