አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተማሪ ደቻሳ ብርሃኑ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ካስፈተናቸው ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ነው።
የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪው ደቻሳ ጊዜውን በአግባቡ ጥናት ላይ በማዋሉ እና ፈተና ከመድረሱ በፊት በቂ ዝግጅት በማድረጉ ከ600 ፤ 562 ነጥብ በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
ለፈተና ያደረገው ዝግጅት ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት ከፈተናው በፊት አስቀድሞ እንዲያውቅ እንዳደረገ የሚናገረው ተማሪ ደቻሳ÷ 530 ለማምጣት አቅዶ 562 በማምጣት ከእቅዱ በላይ ማሳካቱን ጠቁሟል። ለዚህም ከራሱ ጥረት በተጨማሪ የቤተሰቦቹ እና መምህራን ድጋፍ እንዳገዘው አንስቷል።
ደቻሳ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ የሀገሩን ስም የማስጠራት ዓላማ እንዳለው እና አስትሮ ፊዚክስ የትምህርት ዘርፍን ለማጥናት እንዳቀደ ተናግሯል።
እናቱ ወ/ሮ ዓይናለም መኮንን እና አባቱ ብርሃኑ ሀተኡ አጋዥ መጻሕፍትን ከመግዛት እና ለትምህርቱ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ጀምሮ ያደረጉለት እገዛ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ምክንያት እንደሆነለትም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጿል።
የደቻሳ ወላጆች በሰጡት አስተያየት÷ ልጃቸው ከማኅበራዊ ሚዲያ ርቆ ጊዜውን በጥናት እንዲያሳልፍ በማሰብ በቤት ውስጥ የነበረውን የኢንተርኔት አገልግሎት በማቋረጥ ትምህርቱ ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርግ ማገዛቸውን ተናግረዋል።
በጅማ ከተማ ዘንድሮ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛው ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ደቻሳ ብርሃኑ መሆኑም ተገልጿል።
በወርቅአፈራው ያለው
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook WMCC
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!