Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያሳየው ድጋፍ ለሀገራዊ የልማት ግቦች ያለውን መሻት ያሳያል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ ያሳየው ሕዝባዊ ድጋፍ ለሀገራዊ የልማት ግቦች ያለውን መሻት የሚያሳይ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የታታሪ ሕዝቦች አምባ፣ የእንቁ ባህላዊ እሴቶች መገኛ፣ የበርበሬ አምራቾቹ እና የእንሰት ወዳጆቹ ምድር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሕዳሴ መጠናቀቅ የልማት ሰንደቁን በድል አውለብልቧል ብለዋል።

የሕዳሴ ግድቡ የተጠናቀቀው ተባብረው በሰሩ ክንዶች፣ በብስለት በተመሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች፣ በተደመረ የሀገር ሃብት እና ትውልዳዊ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ዛሬ የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ክልሉ የእስከ ዛሬ ስኬቶችን እሴት በማድረግ ለታላላቅ ሀገራዊ የልማት ግቦቻችን ያለውን መሻት ያሳየ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

ለኢትዮጵያ ልዕልና ከላብ እስከ ደም ጠብታ የመታገል እንዲሁም ሀገር በምትፈልገን በሁሉም የልማት ሰልፎች ፊት ቀድሞ የመገኘት የጋራ አቋምን ዛሬ በድጋፍ ሰልፉ አይተናል ነው ያሉት፡፡

የሕዳሴን ድል መርህ እና አርዓያ ያደረገ ልማት ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንደሚጠበቅ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

Exit mobile version