Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሕዳሴ ግድብ የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የጎላ ፋይዳ አለው – ፕሬዚዳንት ታዬ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የጎላ ፋይዳ አለው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።

በተባበሩት መንግሥታት 80ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከጠቅላላ ጉባዔው ፕሬዚዳንት አናሌና ቤርቦክ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በወቅታዊ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች እና በባለብዙ ወገን ግንኙነት ላይ እያሳረፈ ስላለው ተጽዕኖ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በወቅቱ እንዳሉት፤ የባለብዙ ወገን ግንኙነት እና የጋራ ደኀንነት መርሆዎችን ለማስጠበቅ የተቀናጀ ጥረትን ማጠናከር ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ያስመረቀችው የሕዳሴ ግድብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ በተለይም ንጹህ የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ የተባበሩት መንግስታትን ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።

የሕዳሴ ግድቡ እና ሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮችን የበለጠ ለማጠናከር መልካም ዕድል ይዘው ይመጣሉ ነው ያሉት።

አናሌና ቤርቦክ በበኩላቸው የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መርሆችን ማክበር እና መጠበቅ ለዓለም ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ልማት፣ ቀጣናዊ ሰላም እና ደኀንነትን ጨምሮ በተለያዩ ቀጣናዊ የትኩረት መስኮች ላይ ተወያይቷል።

Exit mobile version