Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ቁጥር – 4 መግለጫ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አራተኛ ስብሰባውን መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

በተሻሻለው የባንኩ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1359/2025፣ አንቀጽ 23፣ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት የተቋቋመው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ከባንኩ ዋጋን ከማረጋጋት ቀዳሚ ዓላማ ጋር የተጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ እያቀረበ ያስጸድቃል፡፡

በዚህ ረገድ፣ ኮሚቴው የኢትዮጵያን የዋጋ ግሽበት፣ የፊስካል፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናንስ ዘርፍ አዝማሚያዎችን፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመልካቾችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ አንደምታ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ይገመግማል፡፡

ከእነዚህ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ግምገማዎችና የቅርብ ጊዜ የወደፊት ትንበያዎች በመነሣትም በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረጉ የፖሊሲ ምክረ-ሐሳቦችን ያቀርባል፡፡

 

በዚሁ መሠረት፤ ኮሚቴው በውይይቱ ያካተታቸው ዐበይት ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡-

 

 

 

 

 

 

 

ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች፡- የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ካለፈው ትንበያ በተወሰነ መልኩ ከፍ እንደሚል፣ እ.ኤ.አ በ2025 ዕድገቱ 3.0 በመቶ፤ በ2026 ደግሞ 3.1 በመቶ እንደሚሆን የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) መረጃ ያመላክታል፡፡ ይህም የሆነው ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚኖር፣ በከፊል ከአሜሪካን ዶላር ዋጋ መዳከም ጋር ተያይዞ የተሻሻለ የፋይናንስ ሁኔታ እንደሚፈጠር እንዲሁም በብዙ ትላልቅ ኢኮኖሚዎች ዘንድ የፊስካል ዕድገት እንደሚኖር ታሳቢ በመደረጉ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ፣ የዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት እ.ኤ.አ በ2025 ወደ 4.2 በመቶ ፣ እ.ኤ.አ በ2026 ደግሞ ወደ 3.6 በመቶ ዝቅ እንደሚል ይገመታል፡፡ ይህም የፍላጎት መቀዛቀዝንና የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆልን የሚያመለክት ነው፡፡ ሆኖም፣ የታሪፍ መጨመርና የአቅርቦት እጥረት በአሜሪካን ኢኮኖሚ ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድርና እ.ኤ.አ. በ2025 ሁለተኛ አጋማሽ ለዋጋ ግሽበት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይገመታል፡፡

 

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ግምገማና የውሳኔ ሐሳብ፡-

በሀገራችን የዋጋ ግሽበት በተከታታይ እየቀነሰ መምጣቱ አበረታች ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን ከሚጠበቀው የነጠላ አሃዝ አኳያ ከፍ ያለ መሆኑን ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡ በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየወሰደ ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን ማስቀጠሉ የዋጋ ግሽበቱን ለማርገብ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ኮሚቴው በጽኑ ያምናል፡፡ በባንኮች ዓመታዊ የብድር ዕድገት ላይ የተጣለዉ ገደብ መነሣት ባንኩ ከሚከተለዉ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ አንጻር አግባብ መሆኑን ኮሚቴው ቢገነዘብም፣ አካሄዱ ከፍተኛ ትኩረት እና ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህም የሆነዉ በዋናነት ልቅ የገንዘብ ፖሊሲ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከልና የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህም ግምገማ በመነሣት ኮሚቴው ከዚህ የሚከተሉትን የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ለቦርድ አቅርቦ አስወስኗል፡-

አንደኛ፡- የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን (National Bank Bate) አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይ፣ ብሔራዊ ባንክ ለሚሰጣቸው የተቀማጭ ሂሳብ አገልግሎት (standing deposit facility)፣እና የብድር አገልግሎት (standing lending facility) የሚከፈሉ የወለድ ተመኖች ባሉበት እንዲቀጥሉ፣ እንዲሁም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ምጣኔ በነበረበት እንዲቆይ ተወስኗል፡፡

ሁለተኛ፡- የባንኮች የብድር ዕድገት ገደብ መነሣት የብሔራዊ ባንክን የገንዘብ ፖሊሲ አቋም ለማመልከትና የገንዘብ ፖሊሲ መዋቅሩን የተሻለ ለማድረግ እንደሚረዳ ቢታመንም፣ አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ግሽበት የመርገብ አዝማሚያ ለማስቀጠልና የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለመጠበቅ በመስከረም ወር ላይ ሊነሣ ይችላል ተብሎ የተገመተዉ የባንኮች ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣሪያን ሙሉ ለሙሉ ከማንሣት ይልቅ ገደቡ ለጊዜው ከ18 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ እንዲል ተወስኗል፡፡ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ይህንን ጉዳይ በቀጣይ ስብሰባዎቹ ገምግሞ የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

ሶስተኛ፡- ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበቱ በሚፈለገው ልክ እንዲሆን ለማስቻል እንደ አስፈላጊነቱ ገበያ-መር የሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን በተናጠልም ሆነ በቅንጅት በቀጣይነት የሚጠቀም ይሆናል፡፡ እነዚህ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች የብሔራዊ ባንክ የወለድ ተመን፣ ከባንኮች ጋር የሚደረግ የገንዘብ ግብይት (Open Market Operations)፣ የውጭ ምንዛሪ ገበያ (foreign exchange interventions) እንዲሁም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ምጣኔ ይሆናሉ፡፡

በመጨረሻም ቀጣዩ የኮሚቴው ስብሰባ ታህሳስ ወር 2018 እንዲሆን ተወስኗል፡፡

 

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

መስከረም 19 ቀን 2018

Exit mobile version