አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-
እንኳን ለኢሬቻ መልካ በሰላም አደረሳችሁ
ኢሬቻ የኦሮሞ የምስጋና ስርዓት ነው፡፡ ኦሮሞ የሰው ዘር አፍርቶ የሚባዛው የተዘራው ሞቶ በመነሣት ፍሬ የሚያፈራው በፈጣሪ ድጋፍና እርዳታ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህ ነው ኢሬቻ ሲደርስ ኦሮሞ ልበ ንፁህ የሆነውን ታላቅ ፈጣሪ ላደረገለት ሁሉ በማመስገን ለሚመጣው ጊዜ ደግሞ ምህረትን በመለመን ውዳሴ ያቀርባል፡፡
በጥንት የኦሮሞ ፍልስፍና ውስጥ ኦሮሞ ለውሃ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ ውሃ የንጽህና ምንጭ ፣ የፍጥረትና የህይወት መሠረት ነው ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህም ነው ሲፀልይ ፈጣሪ አምላክ ፣ የፍጥረታት አምላክ ፣ የቡርቃ ወላቡ (የላቡ ምንጭ) አምላክ ብሎ ነው የሚፀልየው፡፡
የዘንድሮው ኢሬቻ ኢትዮጵያ የዜጎቿን የኢነርጂ ፍላጎት ለማሟላት የዓባይን ወንዝ በመገደብ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ባስመረቀችበት ማግስት የሚከበር መሆኑ ደስታችንን ድርብ ያደርገዋል፡፡ እንኳን ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ አለን!
ኦሮሞ መልካ የሌለው ህዝብ ራስ እንደሌለው ህዝብ ነው እንደሚል የባህር በር የሌላት አገር ኑሮ የሌላት አገር ናት ብለን ለህዝባችን ብልጽግና ስንል በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት እየሠራን እንገኛለን፡፡ በዚህ ረገድ እያደረግን ያለነው እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘት ላይ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት አዲስ እሳቤ በሆነው የመደመር ፍልስፍና በመመራት አገር ያላትን ሀብት፣ ልምድና እውቀት ከህዝባችን ጋር በመሆን ቁርጠኛና በሳል አመራር በመስጠት ፣ ፈጣሪም አግዞን በበርካታ ችግሮች ውስጥ ሆነን አስደናቂ ለውጦችን አስመዝግበናል፡፡
በ2018 ዓመተ ምህረትም የኢሬቻ እሴቶች የሆኑትን ሰላም፣ ምህረትና አንድነትን አጥብቀን በመያዝ የአገራችንን ማንሠራራት ለማረጋገጥ በፈተናዎች ሳንበገር ተግተን እንድንሠራ አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡
በድጋሚ የመከናወን ኢሬቻ ይሁልን እላለሁ!
መልካው ሰላም ይሁን! ገዳው የጥጋብና የስኬት ይሁን!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ፣ በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 23፤ 2018