Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል በድምቀት እንዲከበር አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመሰገኑ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል በድምቀት እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ከተማ ሀርሰዴ ሐይቅ “ኢሬቻ ለሀገር ማንሠራራት” በሚል መሪ ሃሳብ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶች እና አርሶ አደሮች ታድመዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ ባስተላለፉት መልዕክት ÷ የሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
ኢሬቻ የፍቅር፣የአብሮነትና የሰላም በዓል ነው ያሉት አቶ ሽመልስ ÷ የኢሬቻ በዓል በድምቀት እንዲከበር አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል፡፡
በዚህም መሰረትም የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር፣ ወጣቶች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢሬቻ በዓልን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል፡፡
የኢሬቻ ሀርሰዴ ‘የኢሬፈና’ (ምስጋና የማቅረብ) ሥነ ሥርዓት በአባገዳዎች ምርቃት በቢሾፍቱ ሀርሰዴ ሐይቅ ተከናውኗል፡፡
አባገዳዎችና ሃደሲንቄዎች በእጃቸው እርጥብ ሳር በመያዝ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን በማብሰር መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁ ሁሉን ነገር ለፈጠረ አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበትና መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪን የሚለመንበት በዓል ነው፡፡
Exit mobile version