አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ለመጪው ትውልድ ሰፊ ትኩረት በመስጠት በሕጻናት እድገትና ትምህርት ላይ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትና የፌዴሬሽን ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ÷ በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት በማህበራዊ ዘርፍ በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
በትውልዶች ውስጥ የሚስተዋለው የእሴት መሸርሸር ዋነኛ መነሻ የትምህርት ጥራት ችግር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም መንግስት የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ ማድረጉን ነው ያስረዱት፡፡
ትምህርት ለትውልድ በሚል መሪ ሃሳብ ማሕበረሰቡን በማንቀሳቀስ የትምህርት ተደራሽነትን የማረጋገጥ ሥራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ተማሪዎች በት/ቤት ምገባ መርሐ ግብር ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ ማድረግ መቻሉን አንስተው ÷ ይህ ጉልህ ተግባር በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር እውቅና እንደተሰጠው ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን መነሻ በማድረግ ክፍተቶችን የመሙላት ሥራ መከናወኑን ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ ÷ በሽታን ከመከላከል ባለፈ አክሞ ማዳን ላይ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል፡፡
የሕክምና መሳሪያዎችን እና መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከፍተኛ ውጤት እንደተገኘም አመልክተዋል።
መንግስት በሚያከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ዋና መገለጫው አካታችነት መሆኑን ጠቅሰው ÷ በዚህም የሕጻናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን እንዲሁም የሀገር ባለውለታዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡
የወጣቶችን ክህሎት በማጎልበት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም አስገንዝበዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት