Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሙስና እና ሌብነትን ለማስወገድ በምናደርገው ጥረት ሥርዓቶቻችንን ማጠናከራችንን እንቀጥላለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሙስናን እና ሌብነትን ለማስወገድ በምናደርገው ጥረት ሥርዓቶቻችንን ማጠናከራችንን እንቀጥላለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

7ኛው ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የ7ኛው የታማኝ ግብር ከፋይ እውቅና ሥነ ሥርዓት ተሸላሚዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ግብር ከፋዮች የሚያዋጡት ግብር ለጋራ እድገትና ለሕዝባዊ ጠቀሜታ በሚውሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚውል ቃል መገባቱን አስታውሰው፥ ዛሬ በከተማችን ኮሪደሮች የሚታየው ለውጥ ለዚያ ቃላችን ሕያው ምስክር ሆኖ ይታያል ነው ያሉት።

የዛሬ ጥረታችሁ የነገን ትውልድ የተሻለ መፃኢ እድል እየቀረፀ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ ሙስናን እና ሌብነትን ለማስወገድ በምናደርገው ጥረት ሥርዓቶቻችንን ማጠናከራችንን እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሂደት ግብር ከፋዮች እንደ ሙስና እና ሌብነት ባሉ ጎጂ ተግባራት የተሠማሩ ሰዎችን ባለመተባበር መንግስት ለሚያደርገው ጥረት እገዛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ግልጽ፣ ተጠያቂነት የሰፈነባትና የበለጸገች ሀገር በጋራ እንገነባለንም ነው ያሉት፡፡

Exit mobile version