አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመደመር መንግሥት መጽሐፍ ሽያጭ የተገኘ ገቢን በሀምበሪቾ ተራራ ሥር የማረፊያ ግንባታ እንዲገነባ በስጦታ አበርክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶስት ወራት በፊት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን ጎብኝተው በገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ ሞዴል የገጠር መንደሮችን ጨምሮ ዓመታዊውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡
በጉብኝታቸው ወቅት የሀምበሪቾ ተራራ 777 ደረጃዎችን ወጥተው ለከምባታ ዞን አስተዳደር ደረጃዎቹን ጨምረው እንዲገነቡ የቤት ሥራ ሰጥተው ነበር የተመለሱት።
በሶስት ወራት ውስጥ የቤት ሥራውን አከናውነው የሀምበሪቾ ተራራ ዳግም 777 ክፍልን እውን በማድረግ በድምሩ ከ1 ሺህ 500 ደረጃዎች በላይ በማድረስ አስደናቂው የተራራ ላይ እይታ ድረስ ገንብተው አጠናቅቀዋል።
ለክልሉ ቁርጠኝነት እና ውጤት እውቅና ለመስጠትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከመደመር መንግሥት መጽሐፍ ሽያጭ የተገኘ ገቢን በሀምበሪቾ ተራራ ሥር የማረፊያ ግንባታ ይገነባ ዘንድ ስጦታ አበርክተዋል።
ይህም አካባቢው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትዕይንታዊ የቱሪዝም መዳረሻነት መጎልበት የበለጠ የሚያገለግል ስለመሆኑ ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡