አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ‘ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጲያ ሕዳሴ’ በሚል መሪ ሀሳብ ሰኞ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይከበራል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ሠንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር መንግሥትና ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ሥልጣን፣ ነፃነት፣ ዕድገትና ማሕበረሰባዊ ትስስር መፍጠሪያ መሣሪያ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ የታተመ የሀገራዊ አንድነትና ነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ እንደሆነ ጠቁሟል።
ጀግኖች አያቶቻችን ወራሪዎችን አሸንፈው ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነውን ሠንደቅ ዓላማ የሕይወት መስዋዕትን ከፍለው ለአዲሱ ትውልድ ማስረከባቸውን በማንሳት ይህንኑ መሠረት በማድረግ ሠንደቅ ዓላማ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት የሚከበር ታላቅ ሀገራዊ በዓል መሆኑ ተመላክቷል።
በመሆኑም የሀገራችንን ሠንደቅ ዓላማ ክብርና ተገቢውን ከፍታ አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሀገራዊ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን ማስቀጠል፤ ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት በማጽናት የሀገራችንን የዕድገት ከፍታ ማረጋገጥ ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነት እንደሆነ አብራርቷል።
የብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በሠንደቅ ዓላማ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 863/2006 (እንደተሻሻለው) አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ መጀመሪያ ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ተደንግጓል።
በዚህ ዓመትም ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታን በዋጀ መልኩ ለ18ኛ ጊዜ ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር ተገናዝቦና የኢትዮጵያን ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራትና ማንሰራራት በሚያረጋግጡ ውይይቶች ታጅቦ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መሪነት በመላው ሀገሪቱ እንደሚከበር አስታውቋል።
በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኤምባሲዎችና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ላይ ሠንደቅ ዓላማ በመስቀልና በሠንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር መግለጫው አመልክቷል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!