አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ባካሄደው 49ኛ መደበኛ ስብሰባው የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ ደንብ ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ተወያይቷል፡፡
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን ከዓለም አቀፍ ማዕቀፎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ለሰላማዊ መንገድ ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነት እንዲኖረው ተደርጎ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በምግብ ዋስትና፣ በጤና አገልግሎት እንዲሁም በሳይንስና ምርምር ዘርፎች ላይ ለመጠቀም የምታከናውናቸውን ተግባራት የሚያስተባብር ይሆናል፡፡
ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

