አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እስራኤላውያኑ ኖኣ አርጋቫኚ እና አቪንታን ኦር በሀማስ ከታገቱ ከ738 ቀናት በኋላ ተለቀው በድጋሚ ተገናኝተዋል፡፡
ጥንዶቹ በፈረንጆቹ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ሀገር ሰላም ብለው በምዕራባዊ ኔጌቭ የኖቫ ሙዚቃ ፌሰቲቫልስን እየታደሙ በነበሩበት ወቅት ነው ሀማስ በድንገት በከፈተው ጥቃት በቡድኑ እገታ ውስጥ የወደቁት፡፡
የአቪንታን ፍቅረኛ የነበረችው ኖኣ አርጋቫኒ በድንገት ከተከፈተው የሽብር ጥቃት በኋላ የሀማስ ታጣቂዎች በኃይል ሞተር ሳይክል ላይ እንድትወጣ በማስገደድ ወደ ጋዛ ሲወስዷት የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል በብዛት ተጋርቶ ነበር፡፡
ከአስደንጋጩ ክስተት በኋላ የእስራኤል ኮማንዶ ኃይል በፈረንጆቹ ሰኔ 8 ቀን 2024 በማዕከላዊ ጋዛ ባደረገው ወታደራዊ ዘመቻ የአቪንታን ፍቅረኛ የነበረችው ኖኣ አርጋቫኒን ከሀማስ እገታ ማስለቀቅ ችሏል፡፡
ኖአ ከእገታ ነፃ ብትሆንም በሀማስ እገታ ውስጥ የወደቀውና የት እንዳለ የማይታወቀው ፍቅረኛዋ አለመለቀቁ ደስታዋ ሙሉ እዳይሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ የሀማስ እና እስራኤልን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ከተለቀቁት የመጀመሪያ ሰባት ታጋቾች አንዱ የኖኣ አርጋቫኒ ፍቅረኛ አቪንታን ኦር ሲሆን÷ ጥንዶቹ ከተለያዩ ከሁለት ዓመት በኋላ በድጋሚ መገናኘት ችለዋል፡፡
የፍቅረኛዋን መለቀቅ ተከትሎም ኖኣ በማሕበራዊ ትስስር ገጿ ላይ ባስተላለፈችው መልዕክት÷ ከአቪንታን ጋር የመጨረሻዋን ጊዜ አብረን ካሳለፍን ሁለት ዓመት አልፎናል፤ በጨካኞች እጅም ሁለት የጭንቅ ዓመታትን አሳልፈናል ብላለች፡፡
ከእገታው በኋላ ኖኣ ከሌሎች ታጋች ሴቶች እና ህፃናት ጋር በመሆን በመኖሪያ ቤት ተቀምጠው መቆየታቸውን በመግለጽ ፍቅረኛዋ አቪንታን ኦር ግን በዋሻ ውስጥ ማሳላፉን ተናግራለች፡፡
አቪንታን በህይወት ይኖራል ብዬ አላስብም ነበር ያለችው ኖኣ÷ ነገር ግን ሀማስ በድንገት በለቀቀው ምስል ፍቅረኛዋ በማዕከላዊ ጋዛ በህይወት እንዳለ አረጋግጣ እንደበር ገልፃለች፡፡
የችግሮቹን ጦርነት በግል ብናሸንፍም መላው ዓለም ግን ከኛ ነበር፤ አሁን ግን ፍቅራችንን ከእንደገና የምንጀምርበት ጊዜ ደርሷል ብላለች፡፡
የሰላም ስምምነቱ እንዲደረስ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምስጋና ማቅረቧንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ