Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝማችን አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ቀጥሏል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአስደናቂ ብዝኅ መልኩ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝማችን አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ቀጥሏል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ የባሌ ዞን የመጀመሪያ ቀን ጉብኝት ያሳየን በድንቅ ተፈጥሮ እና በልማት ሥራ እድገት መካከል ያለውን መስተጋብር ነው ብለዋል።

በአስደናቂ ብዝኅ መልኩ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝማችን አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ መቀጠሉን ጠቁመው ÷ ይህ እምቅ አቅም በፓርኩ እምብርት ላይ የተገነባው የዲንሾ ሎጅ በቅርቡ ሲጠናቀቅ የበለጠ ይጠናከራል ነው ያሉት።

በአቅራቢያው በመገንባት ላይ ያለውና በቅርቡ የሚጠናቀቀው የሶፍኡመር ሎጅ ቱሪዝምን የኢኮኖሚያችን ቁልፍ መሪ አድርጎ ያስቀመጠው የኢትዮጵያን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ የሚተገብር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ሎጁ በሶፍኡመር ዋሻ የጎብኝዎችን ቆይታ ከፍ የሚያደርጉ እና የመዝናኛ አገልግሎት መስጫዎች በሶፍኡመር ዋሻ ልማት ፕሮጀክት እገዛ የሚዘጋጁበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በመንገድ መሠረተ ልማት ረገድ የሮቤ-ጎሮ-ሶፍኡመር-ጊኒር መንገድ የማሻሻያ ፕሮጀክት ከፍተኛ አምራች የሆኑትን የምሥራቅ ባሌ እና የባሌ ዞኖችን ምርታቸውን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚያገናኝ ነው።

ይኽ መሥመር ተደራሽነትን እና የኢኮኖሚ ተያያዥነትን ብቻ ሳይሆን እንደሶፍኡመር ዋሻ እና የባሌ ተራሮች ወደ መሰሉት ዐበይት የመስኅብ ሥፍራዎች ጉዞን የሚያሳልጡ ናቸው።

ድርብ አስፋልት ንጣፍ ባለው ከፍ ያለ ደረጃ የተገነባው መንገድ 29 ኪሎሜትር የከተማ እና የገጠር መንገድን የሚያካትት ብሎም ከ12 እስከ 140 ሜትር ርዝመት ያላቸው አምስት ድልድዮች የተሠሩበት ነው።

የቀኑን ጉብኝታቸውን የወይብ ወንዝ የጎርፍ መቆጣጠሪያ ፕሮጀክትን በመመልከት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በሶፍኡመር ዋሻ የሚጓዘውን የወንዙን የውሃ ፍሰት በመቆጣጠር ዓመቱን ሙሉ ወደ ዋሻው የሚደረግ ጉዞ እንዳይስተጓጎል ለማድረግ ብሎም የዋሻውን ሥነ ምኅዳር ለመጠበቅ ታልሞ የተሠራ ነው።

ሁሉም ሥራዎች ቀጣይነት ላለው ልማት ያለንን ጽኑ አቋም እና ተግባር የሚገልጡ ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጽሑፋቸው።

Exit mobile version