አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ እና ድራም የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቿ ሳናይ ታካይቺ የጃፓን የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ተመርጠዋል፡፡
ቀደም ሲል የገዢው ሊብራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ መሆን የሚያስችላቸውን ድምጽ ያገኙት የ64 ዓመቷ ታካይቺ፥ ፓርቲያቸው ከጃፓን ኢኖቬሽን ፓርቲ ጋር የፈጠረውን ጥምረት ተከትሎ ነው ሀገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመምራት እድል ያገኙት፡፡
ሳናይ ታካይቺ መመረጣቸውን ተከትሎ በአምስት ዓመታት ውስጥ ጃፓንን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመምራት የተመረጡ አራተኛ ሰው ሆነዋል፡፡
የዓለም አራተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጃፓን በተለይ በኢኮኖሚ አለመረጋጋት ውስጥ መሆኗ ለተመራጯ ጠቅላይ ሚኒስትር ፈተና እንደሚሆን እየተነገረ ይገኛል፡፡
ትውልዳቸው በጃፓን ናራ ግዛት በፈረንጆቹ 1961 ነበር፡፡ ወደ ፖለቲካ ከመግባታቸው አስቀድሞ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ በመሆን የሰሩ ሲሆን፥ በተለይ በድራም የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነታቸው ይታወቃሉ፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1980ዎቹ ወደ ፖለቲካ ጉዳዮች መሳብ እንደጀመሩ የሚነገርላቸው ታካይቺ፥ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን በማሳደግ በ1992 በተደረገው ምርጫ በግል መወዳደር ችለው ነበር፡፡
በመቀጠል በ1996 የወቅቱን ፓርቲያቸውን ሊብራል ዴሞክራቲክ ፓርቲን የተቀላቀሉ ሲሆን፥ ከዚያ ወዲህ ለ10 ያህል ጊዜ የሀገሪቱ ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታነት እስከ ኢኮኖሚ ደህንነት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ጉዳዮችና የኮሙኒኬሽን ሚኒስትርነትን ጨምሮ ሀገሪቱን በተለያዩ ኃላፊነቶች ማገልገል ችለዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት ምርጫ የፓርቲያቸው መሪ ሆነው ከመመረጣቸው አስቀድሞ በ2021 እና በ2024 ለሁለት ጊዜ ለዚህ ኃላፊነት የተወዳደሩ ቢሆንም ሳይሰምርላቸው ቀርቷል፡፡
ከፖለቲካ ተሳትፏቸው ቀደም ብሎ በቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢነት የሚታወቁት ሳናይ ታካይቺ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በተለያዩ የሙዚቃ ባንዶች ውስጥ በድራም ተጫዋችነት ተሳትፈዋል፡፡
በተለይም ከ10 ዓመት ገደማ በፊት ኤክስ ጃፓን የተሰኘውን የሀገሪቱ ዝነኛ የሮክ ባንድ ሙዚቃ በጃፓን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ሲያቀነቅኑ የሚታይበት ተንቀሳቃሽ ምስል ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያው በስፋት መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
በሙዚቃና በቴሌቪዥን የፕሮግራም አቅራቢነታቸው የሚታወሱትና ባለፉት በርካታ ዓመታት በፖለቲካው በስፋት የሚታወቁት የ64 ዓመቷ ሳናይ ታካይቺ ጃፓንን ለመምራት የመጀመሪያዋ የሀገሪቱ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ