Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፊስካል አስተዳደርን ለማጠናከር፣ የሀገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብን ለማጎልበትና መዋቅራዊ የሪፎርም ስራዎችን ለማፋጠን መንግስት ቁርጠኛ ነው – አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት የፊስካል አስተዳደርን ለማጠናከር፣ የሀገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብን ለማጎልበት እና ቁልፍ መዋቅራዊ የሪፎርም ስራዎች ለማፋጠን ቁርጠኛ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ገለጹ።
በአቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በኢኮኖሚ ሪፎርም ሂደት እና ከአይ ኤም ኤፍ አመራር ጋር ያለውን ቀጣይ አጋርነት በተመለከተ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ እና ከአይ ኤም ኤፍ የአፍሪካ ዲፓርትመንት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2025 የዓለም ባንክ ቡድን እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን የተካሄደ ሲሆን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የወደፊት ትብብር ዙሪያ ያተኮረ ነበር።
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ እንዲሁም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችን ያካተተ ነው።
አቶ አህመድ ሺዴ አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ቀጣይነት ላለው ድጋፍ አመስግነው፣ መንግስት የፊስካል አስተዳደርን ለማጠናከር፣ የሀገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብን ለማጎልበት እና ቁልፍ መዋቅራዊ የሪፎርም ስራዎች ለማፋጠን ያለውን ቁርጠኝነትን በአጽንኦት አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከአይ ኤም ኤፍ ጋር ያላትን የቆየ አጋርነት ከፍ ያለ ግምት ትሰጣለች ያሉት ሚኒስትሩ በማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ የስራ እድል ፈጠራ እና የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል ላይ ያተኮሩ ደፋር የሪፎርም ስራዎችን ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሆነም አስረድተዋል።
የአይ ኤም ኤፍ የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ እነዚህን አላማዎች ለማሳካት አጋዥ ሆነው እንደቀጠሉም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
እየተካሄደ ባለው የሪፎርም ማዕቀፍ ውስጥ ሰፊ የማህበራዊ ጥበቃ እርምጃዎች አካል በመሆን የኢትዮጵያን አወንታዊ የኢኮኖሚ እይታ እና የመንግስት የማህበራዊ ወጪ መጨመርን በተመለከተ ለዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያን የለውጥ ጥረቶች ግስጋሴ እና ስኬት በማጉላት ለስኬቶቹ መነሻ የሚሆኑ በርካታ ቁልፍ ጉዳዮችን አቶ አህመድ ሺዴ ያብራሩ ሲሆን ለስኬቶቹ መነሻ የሆኑ ተግባራትንም አንስተዋል።
በከፍተኛ የመንግስት እርከኖች ጠንካራ ባለቤትነት እና ቁርጠኝነት፣ በሁሉም የመንግስት አካላት ሁሉን አቀፍ ውሳኔ አሰጣጥ እና ትግበራ፣ በጥንቃቄ የተነደፉ ቅደም ተከተል ያላቸው የሪፎርም እርምጃዎችን በሚገባ ማዘጋጀት፣ በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ውጤታማ የግንኙነት እና የማህበራዊ ጥበቃ ዘዴዎች እንዲሁም ከልማት አጋሮች በተለይም ከአይ ኤም ኤፍ፣ ከአለም ባንክ እና ከኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ዋና ዋናዎቹ ተጠቃሽ እርምጃዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዋን የበለጠ ለማራመድ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም እና ዘላቂነት ፋሲሊቲ (Resilience and Sustainability Facility (RSF)) ለማግኘት ያላትን ከፍተኛ ፍላጎትም በአጽንኦት አንስተዋል።
የሁለትዮሽ እና የንግድ አበዳሪዎች ጋር እየተደረገ ስላለው የዕዳ አያያዝ ውይይቶችን በተመለከተ ለአይኤምኤፍ የስራ ሀላፊዎች ወቅታዊ ማብራሪያ የሰጡት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ናቸው።
እስካሁን የተገኘውን አበረታች እድገት በመጥቀስ በዚህ ሂደት ውስጥ የአይ ኤም ኤፍ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አስፈላጊነትን በተመለከተም እንዲሁ አጽንኦት ሰጥተው ገልፀዋል።
የአለም ገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ክፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በአይ ኤም ኤፍ ለሚደገፈው የሪፎርም ፕሮግራም ጠንካራ ትግበራ ከፍተኛ አድናቆት እና ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ እስካሁን የተሰሩ የሪፎርም ጉልህ ስኬቶችን እውቅና ሰጥተው፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት መመዝገቡን፣ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መሄዱን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጠናከር መንግስት የጀመረውን የሪፎርም ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጠናከር ዋና ዳይሬክተሯ እንደሚያበረታቱም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ለውጥ እና የእዳ ማስተካከያ ዘላቂ ጥረቶች ከዋና ዋና የልማት አጋሮች ጋር በቅርበት ለመደገፍ የአለም ገንዘብ ድርጅት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ሊጀመር በታቀደው የአራተኛው የፕሮግራም ግምገማ ወቅት ሁለቱም ወገኖች ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር እና እድገትን እና የማሻሻያ ዕድሎችን በጋራ ለመገምገምም ስምምነት ላይ ተደርሷል።
Exit mobile version