አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ10 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ100 ቀን እቅድ ግምገማ የዓለምን የኢኮኖሚ አዝማሚያ እንዲሁም የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ተመልክቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም የእድገት አዝማሚያን እና አጠቃላይ ምልከታን ያካተተ እንደነበር የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ከዓለም የኢኮኖሚ ልማት አውድ አንጻር ኢትዮጵያ ልዩ ጥንካሬ እና የእድገት ፍጥነት ማሳየቷ ነው የተገለጸው፡፡
በ2017 የበጀት ዓመት የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ አፈፃፀም በጥንካሬው በመቀጠል 9 ነጥብ 2 በመቶ ዓመታዊ የጂዲፒ እድገት አሳይቷል።
ይህም 7 ነጥብ 3 በመቶ በሆነ ጠንካራ የግብርና ውጤት መስፋፋት፣ በ13 በመቶ የኢንዱስትሪ እድገት ብሎም በ7 ነጥብ 5 በመቶ የአገልግሎት ዘርፍ እድገት የተገለጸ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ የጂዲፒ ተዋፅኦም በብዝኃ መሠረት እየያዘ መሄዱን የሚያሳይ ሲሆን÷ ይህም በግብርና 31 ነጥብ 3 በመቶ፣ በኢንደስትሪ 30 ነጥብ 2 በመቶ እና በአገልግሎት 39 ነጥብ 6 በመቶ አስተዋፅኦ የታየ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
እየተካሄዱ በሚገኙ የለውጥ ሥራዎች፣ በመንግሥት እየተከወኑ ባሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እና አዲስ ኢንቨስትመንቶች በመደገፍ በ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ10 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል።

