አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 12፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ጥላሁን ያሚ እና አብዲ ዓለማየሁ ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ 10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ተረኛ ችሎት ከዚህ በፊት አያያዛቸውን በተመለከተ የእስረኞች አስተዳደር ቀርቦ እንዲያብራራ ትእዛዝ መስጠቱን ተከትሎ ችሎቱ የምርመራ ውጤቱን ለመጠባበቅ የተሰየመ ሲሆን፥ ከእስረኞች አስተዳደር ግን ማንም ሰው ሳይገኝ ቀርቷል።
መርማሪ ፖሊስም በጉዳዩ ላይ መረጃ እንደሌለው ጠቅሶ ሌላ ጊዜ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ የሰራቸውን የምርመራ ስራዎች ይፋ አድርጓል።
ተጨማሪ የምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ የተለያዩ የቴክኒክ ማስረጃዎች መሰብሰቡን፣ ሌሎች አባሪዎች እና ግብረ አበሮችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ለችሎቱ አስረድቷል።
አርቲስት ሃጫሉ የተተኮሰበት ሽጉጥም የፎረንሲክ ምርመራ ተደርጎበት የወንጀሉ ፍሬ መሆኑን የሚያሳይ ውጤት እንደደረሰው አብራርቷል።
እንዲሁም የሟች አስክሬን የምርመራ ውጤትን መቀበሉን የገለፀው መርማሪ ፖሊስ፥ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትም የስልክ ልውውጣቸውን እንደላከና ከግድያው በስተጀርባ ያሉ ተጨማሪ ጉዳዮችን በጥንቃቄ እየመረመረ መሆኑን ነው የዘረዘረው።
በተጨማሪም ከጀርባቸው ብዙ አባሪዎች አሉ የሚል ጥርጣሪ ስላለኝ በጥንቃቄ ምርመራውን እያደረኩኝ መሆኑን ተከትሎ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ህጉ መሰረት ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
አንደኛ ተጠርጣሪ ጥላሁን ያሚ በበኩሉ ”ወጥቼ የፀሃይ ብርሃን አላገኘሁም፣ ቅያሪ ልብስ አላገኘሁም፣ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ይስልጥኝ፣ ካተናዬም እንዲወልቅና ከፖሊስ ጣቢያ ወደ ማረሚያ ቤት እንድዛወር ይፍቀድልኝ” ሲል አቤቱታ አቅርቧል።
ሁለተኛ ተጠርጣሪ አብዲ ዓለማየሁ ”ወደ ውጭ ወጥቼ የፀሃይ ብርሃን እንዳገኝ ፍርድ ቤቱ ይፍቀድልኝ” ሲል አመልክቷል።
ፍርድ ቤቱም አያያዛቸውን በተመለከተ በቂ የፀሃይ ብርሃን እንዲያገኙ እንዲደረግ እና በዛሬው ትእዛዝ ያልቀረቡ የማረሚያ ቤት አስተዳደር ተወካዮች ለምን ቀርበው እንዳላብራሩ እንዲያስረዱ በድጋሚ እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል።
ለመርማሪ ፖሊስም ተጨማሪ የምርመራ ስራዎችን አከናውኖ እንዲመጣ 10 ቀን ፈቅዶለታል።
በታሪክ አዱኛ

