Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሩብ ዓመቱ በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል – ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል አሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፡፡

ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የ2018 የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን አስመልክተው ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

በሪፖርታቸውም በ2017 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት 9 ነጥብ 2 በመቶ፣ ግብርና 7 ነጥብ 3 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 13 በመቶ እና የአገልግሎት ዘርፍ 7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ከኢኮኖሚ መጠን አንጻርም 15 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር መድረስ መቻሉን ጠቁመው ÷ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ እድገት የታየበት ነው ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ እድገቱ ጥራት ያለው ነው ያሉት ሚኒስትሯ÷ ይህ ማለትም ከአምራቾች የሚመነጭ፣ የሥራ እድል የሚፈጥር እና እሴት የሚጨምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አፈጻጸሙም የኢትዮጵያ መዋቅራዊ ሽግግር ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን አመላካች ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የአገልግሎት ዘርፉ ጥራትና ቅልጥፍና በእጅጉ እየተሻሻለ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሯ ÷ የኤክስፖርት ንግድም አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 10 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያድግ መተንበዩን ጠቁመው÷ ትንበያው እንዲሳካ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ ቀመጠል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በተለይም የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ ዲጂታላይዜሽን፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እና ሌሎችን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት፡፡

ገቢን መጨመር እና ትልልቅ ኢንቨስመንቶችን መሳብ እንዲሁም የግልና የመንግስት ዘርፉን ትብብር በማሳደግ ምርታማነትን መጨመር እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

የልማት ፋይናንስ መሻሻሉን ጠቁመው ÷ለአብነትም ንግድ ባንኮች የብድር ጣሪያ አምና ከነበረበት 18 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማለቱን እና ባንኮች ይፈጽሙት የነበረው 20 በመቶ የግምጃ ቤት ቦንድ ግዥ እንዲቀር መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ኢኮኖሚው በተሻለ ሁኔታ እንደሚያድግ መተንበዩ ለዓለም ብሎም ለንግድ አጋሮች ግንኙነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች 12 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እያረሱ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

የግብርና ምርት ስብጥር እየተቀየረ ነው፤ የስጋና ወተት ምርት መጨመር እና የአዳዲስ መዳረሻዎች መስፋት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል፡፡

በተያዘው ዓመት እስካሁን 26 ነጥብ 32 ሚሊየን ሄክታር በዘር የተሸፈነ ሲሆን ÷ ከዚህ ውስጥም 23 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታሩ ሰብል ፤ 2 ነጥብ 45 ሚሊየኑ ደግሞ ሆርቲ ካልቸር ነው ብለዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ሥራዎች የተሻለ ውጤት መመዝገቡን እና ይህም ኢትዮጵያ ወደ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የምታደርገውን ፈጣን ሒደት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version