Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

323 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ሶስት ወራት የተሰበሰበው ገቢ 323 ቢሊየን ብር ደርሷል አሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፡፡

ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የ2018 የመጀመሪያ 100 ቀናት አፈጻጸምን አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት÷ በሩብ ዓመቱ ከተለያዩ ዘርፎች ገቢን ለመሰብሰብ በትኩረት መሰራቱን አመልክተዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ባለፉት ሶስት ወራት የተሰበሰበው የፌደራል መንግስት ገቢ 323 ቢሊየን ብር ደርሷል ነው ያሉት፡፡

ይህ አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ112 በመቶ ጭማሪ ያለው ሲሆን÷ በወቅቱ የተሰበሰበው ገቢ 152 ቢሊየን ብር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ወራት ከወርቅ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰው ÷ ከቡና ደግሞ 763 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

የሃዋላ ፍሰት 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን÷ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ደግሞ 961 ሚሊየን ዶላር ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋለ ሚኒስትሯ፡፡

አጠቃላይ ተቀማጭ ሃብት 3 ነጥብ 73 ትሪሊየን ብር መድረሱን ገልጸው÷ ለዘርፎች የሚሰጠው የብድር መጠን ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version