አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር የኢነርጂ ዘርፉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው አሉ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‘የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምልከታ በኮይሻ’ በሚል ርዕስ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ውይይት በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አድርገዋል።
ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፤ የኮይሻ ፕሮጀክት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
ከዚህ ቀደም የነበሩ መሪዎች የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት ለመጠቀም ሙከራ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ ነገር ግን ሙከራቸው በብልሃት የታጀበ ባለመሆኑ ትልቅ ነጥብ ጥለን በሃብቱ ሳንጠቀም ቆይተናል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ብስለት የተሞላበትና ሙሉ ዕይታ የኢትዮጵያን እምቅ አቅም አሰናስኖ ጥቅም ላይ ለማዋል ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን በመስኖ እና በኃይል የመጣው ውጤት የኢትዮጵያን ከፍታ በተጨባጭ ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ሊሆን የቻለው በልዩ አመራር እና ብስለት በተሞላበት አካሄድ መሆኑን ዘርፉን እንደሚመራ ሰው ለመመስከር እፈልጋለሁ ነው ያሉት።
ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እየመጣ ላለው መዋቅራዊ ለውጥ የኢነርጂ ዘርፉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ለሚደረገው የኢትዮጵያ ብልጽግና ጉዞ የኮይሻ ፕሮጀክትን ጨምሮ የኢነርጂ ዘርፉ የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
የኮይሻ ፕሮጀክት ከኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ ሌሎች በረከቶችንም ይዞ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዓሣ ሃብት ልማት፣ በቱሪዝም እና የጎርፍ አደጋን በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የኮይሻ ፕሮጀክትን ከጨበራ ጩርጩራ፣ ሃላላ ኬላ እና ጊቤ ሶስት ጋር በማስተሳሰር የቱሪዝም ስበት ማዕከልነቱን ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ኮይሻ ውሃ መያዝ ሲጀምር በየወቅቱ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑት የኦሞራቴ እና ዳሰነች አካባቢዎች ከችግሩ እንደሚላቀቁ አመልክተዋል።

