አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እውነተኛውን የሀገራችን ለውጥ የሚመራው የራሳችን ጽናት፣ ፈጠራ እና የሥራ ትጋት ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በምስራቅ ሸዋ ዞን በክረምት የስንዴ ምርት ሥራዎች የተገኘውን ውጤት የምርት አሰባሰቡን በመመልከት ለመገምገም እና የበጋ ስንዴ ሥራ ማስጀመር ላይ ያተኮረ ጉብኝት አድርገዋል።
በአካባቢ የሙዝ፣ ፓፓያ እና ዓሣ ክላስተር ሥራዎች መመልከታቸውንም በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ አመላክተዋል።
ነባሩ ባሕላዊ የግብርና ዘዴ አሁንም ያለ ቢሆንም በሰፊው ለማረስ የሚያስችለው ሜካናይዜሽን እያደገ በመሄዱ የአካባቢውን የግብርና ብቁነት እና ምርታማነት እያሳደገ ይገኛልም ነው ያሉት።
ወደኋላ መለስ ብለን የነበረውን አሰራር ስንገመግም እነዚህን መሰል ዘመናዊ ዘዴዎችን ከብዙ ዓመታት በፊት እንደ ሀገር ጀምረን ቢሆን ኖሮ የግብርና ምርታችን በከፍተኛ ደረጃ የተለየ ይሆን እንደነበር እንረዳለን ሲሉም ገልጸዋል።
ዛሬ ከዓመት ወደ አመት እየጨመረ የሚሄድ ምርታማነት እየተመለከትን እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ለማደግ ምንም አይነት የውጭ ድጋፍ አይመጣም፤ እውነተኛውን የሀገራችን ለውጥ የሚመራው የራሳችን ጽናት፣ ፈጠራ እና የሥራ ትጋት ነው ብለዋል።

