Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ነው የምክትል ከንቲባ ሹመትን ያፀደቀው።

በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ወይዘሮ አዳነች አቤቤን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾሟል።

ቀደም ሲል በምክትል ከንቲባነት ሲያገለግሉ የነበሩት ኢንጂነር ታከለ ኡማ የኢፌዴሪ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መሾማቸውን ተከትሎ ነው በምትካቸው ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የተሾሙት።

አዲስ የተሾሙት ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም በምክር ቤቱ ቀርበው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

ወይዘሮ አዳነች ቀደም ሲል በኢፌዴሪ የገቢዎች ሚኒስትርነት በመቀጠልም በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ከዚያ ቀደም ብሎም በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ላይ ሰርተዋል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በምክር ቤቱ ቀርበው ባደረጉት ንግግርም፥ አዲስ አበባ እንደ ስሟ እና ዘመናዊ እንድትሆን ብዙ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

ለዚህም ለቀድሞ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና ለካቢኔያቸው ምስጋና ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በቀጣይ ጊዜያትም አዲስ አበባን ለማስዋብና ሁሉም ዜጋ እኩል የሚገለገልባት ከተማ ለማድረግ፣ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ለማሟላት፣ የተጀመሩ በርካታ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል እና አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በከተማዋ ድህነትን ለመቀነስ እና የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራበት መሆኑንም ገልፀዋል።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በመቀጠልም አቶ ዣንጥራር አባይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ሆነው እንዲሾሙ ለምክር ቤቱ በእጩነት አቅርበዋል።

ምክር ቤቱም ሹመቱን በመቀበል አቶ ዣንጥራር አባይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አድርጎ ሾሟል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version