Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የግብርናው ለውጥ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከተረጂነት እንደምትወጣ አመላካች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በግብርና ዘርፍ የመጣው ለውጥ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከተረጂነት እንደምትወጣ አመላካች ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በትናንትናው ዕለት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የመኸር ስንዴ ምርት አሰባሰብን በመጎብኘት የበጋ ስንዴ ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂደዋል።

ጉብኝቱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ በዞኑ እየተካሄደ ያለው የስንዴ፣ ሙዝ እና ፓፓያ ልማት ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

በሴፍቲኔት ታቅፎ ሲረዳ የነበረው አካባቢው አሁን ላይ አስገራሚ የግብርና ልማት እየተካሄደበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአካባቢው በኮምባይነሮች የስንዴ ምርት እየተሰበሰበ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን መሬቱን ለበጋ የስንዴ ልማት የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል።

አካባቢው ውሃ አጠር እና ሞቃታማ ቢሆንም የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም በተሰራው ስራ አርሶ አደሩ ከተረጂነት ወደ አምራችነት እየተሸጋገረ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት፡፡

የአካባቢው ልማት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የሰው ሃብት እና የተፈጥሮ ጸጋን ይዛ መለመን የለባትም ያሉትን በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በአካባቢው አትክልትና ፍራፍሬ ጭምር እየለማ መሆኑን ገልጸው፤ ሙዝ እና ፓፓያ ማምረት መጀመሩ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ተናግረዋል።

የምርት መጨመርን ተከትሎ ማነቆ የነበረው የገበያ ትስስር በመፈታቱ አርሶ አደሩ ምርቱን እዛው ባለበት መሸጥ መጀመሩ ወሳኝ ርምጃ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአካባቢው ልማት የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ማንሰራራት አይቀሬ እንደሆነ ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በግብርና ዘርፍ የመጣው ለውጥ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከተረጂነት እንደምትወጣ አመላካች ነው ብለዋል።

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version