አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ሶስት ወራት ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ከ4 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ የሥራ ማስኬጃ ብድርና የማምረቻ መሳሪያ ተሰራጭቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኑኬሽን ተ/ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮቤል አሕመድ እንዳሉት÷ በ2018 በጀት ዓመት የአምራች ኢንተርፕራይዞችን ሁለንተናዊ አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በተለይም ኢንተርፕራይዞች ከብድርና መስሪያ ቦታ ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የዘርፉን የአሰራር ሥርዓት ለማሻሻል፣ የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግና ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲያመርቱ ለማስቻል አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ለኢንተርፕራይዞች የሥራ ማስኬጃ ብድር አቅርቦትና የማምረቻ ማሽን በሊዝ ፋይናንስ አማካኝነት ተደራሽ ከማደረግ አንጻር አበረታች ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ለ388 አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የሥራ ማስኬጃ ብድር ተሰራጭቷል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ለ277 ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ከ877 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የማምረቻ መሳሪያዎችን ማሰራጨት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የቁጠባ ባሕልን በማሳደግ የፋይናንስ ተቋማትን የማበደር እና የኢንተርፕራይዞችን የመበደር አቅም ለማሳደግ በትኩረት መሰራቱንም ነው የገለጹት፡፡
በመላኩ ገድፍ

