አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባሳለፍነው ሰኔ ወር መንገደኞችንና የበረራ ሰራተኞችን ጨምሮ 242 ሰዎችን የያዘ አውሮፕላን ተከስክሶ 241 ያህሉ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡
ከዚያ አስከፊ አደጋ በህይወት የተረፈው የ39 ዓመቱ ቪስዋሽኩመር ራሜሽ፥ ተዓምር እንደሆነ በገለጸው ሁኔታ ከአደጋው ተርፎ በህይወት በመቆየቱ እድለኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ራሜሽ ወንድሙን ጨምሮ በአውሮፕላኑ የተሳፈሩ ሌሎች ሰዎች በሙሉ ከሞቱበት አስከፊ አደጋ ተርፎ ዛሬ ላይ በህይወት ቢኖርም፥ በድኅረ አደጋ ጭንቀት እየተሰቃየ ይገኛል፡፡
በወቅቱ የህክምና ድጋፍ ተደርጎለት እንግሊዝ ሌስተር ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ቢመለስም፥ በዚሁ የድኅረ አደጋ ጭንቀት የስነ ልቦና ችግር ምክንያት ከባለቤቱም ሆነ ከ4 ዓመት ልጁ ጋር ለመነጋገር ተቸግሯል፡፡
“በቤቴ ውስጥ ብቸኛ ሰው ሆኛለሁ፥ ከባለቤቴም ከልጄም ጋር ማውራት አልቻልኩም፥ ከሰው ተነጥዬ ባዶ ክፍል ውስጥ ለብቻዬ ነው ያለሁት” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡
“በአደጋው ወቅት ስለነበረው ሁኔታ መናገር በጣም ከባድ ነው፥ ምንም መናገር አልችልም፥ከማንም ጋር መነጋገር አልፈልግም፥ ሌሊት እንቅልፍ የለኝም ሲል” እሱም ሆነ ቤተሰቡ ያሉበት ሁኔታ በስቃይ የተሞላ እንደሆነ ገልጿል፡፡
አዕምሮው ሰላም ከማጣቱ ባሻገር ከአደጋው ለመሸሽ ሲሞክር እግሩና ትከሻውን ጨምሮ በደረሰበት አካላዊ ጉዳት በህመም ላይ መሆኑንም ተናግሯል፡፡
የስነ ልቦና አማካሪዎች በበኩላቸው፥ ራሜሽ ‘ፒቲኤስዲ’ በመባል በሚታወቀው የድኅረ አደጋ ጭንቀት የስነ ልቦና ችግር እየተሰቃየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአደጋው ወቅት በተፈጠሩት ሁኔታዎች ለዚህ ስነ ልቦናዊ ቀውስ መዳረጉንና ቤተሰቦቹም ጭምር በሁኔታው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸው፥ ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ለማገገም ብዙ ጊዜ ሊፈጅበት ይችላል ነው ያሉት፡፡
አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በአየር መንገዱ በአግባቡ ክትትል አልተደረገለትም የሚሉት የስነ ልቦና አማካሪዎቹ፥ የሚመለከታቸው የተቋሙ ኃላፊዎች ቀርበው የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የህንድ አየር መንገድ ለተጎጂው 21 ሺህ 500 ፓውንድ ጊዜያዊ የካሳ ክፍያ መክፈሉ የተገለጸ ሲሆን፥ ከደረሰበት ጉዳት አንጻር ይህ በቂ አለመሆኑን አማካሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

