Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት አንገት የሚያስደፋ ታሪክ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሁላችንንም አንገት የሚያስደፋ ጥቁር ታሪክ ነው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት የተፈፀመበት 5ኛ ዓመት “እንዳይደገም ፤ መቼም አንረሳውም” በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት ታስቦ ውሏል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ መከላከያ ሠራዊትም ሆነ የኢትዮጵያ አርበኞች መስዋዕትነት በመክፈል ሀገር አቆይተዋል።

ሀገር በመጠበቅ ሀገር ለማቆየት ከሰሜን ዕዝ በፊትም ሆነ በኋላ የተከፈሉ መስዋዕትነቶች መኖራቸውን ገልጸው፥ የሰሜን ዕዝ መስዋዕትነትን ልዩ የሚያደርገው በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ መሆኑ ብለዋል።

ዕለቱን መቼም ቢሆን አንረሳውም፤ ሁልጊዜ የምናስታውሰው ነውና የምናከብረውም እንዳይደገም ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፥ ዕለቱ በሕይወት ዘመኔ በጣም ያዘንኩበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ባዕዳን ቢከዱ የሚጠበቅ ነው፤ ወገን ሲከዳ እና ሲጨክን ግን አዕምሮና ልብ የሚሰብር ነው ብለዋል።

ሰሜን ዕዝ የነበረው ሠራዊት በባድመ፣ በዛላንበሳ እና በጾረና የትግራይ ሕዝብ ምሽግ እና አጥር በመሆን ከሻዕቢያ በመጠበቅ ላይ የነበረ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ በመገንባት፣ በግብርና ላይ በመሰማራት ትግራይን ሲያለማ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ነገር ግን በጣም ጥቂት ከሀዲ ቡድን ይሄንን ባለውለታ ሠራዊት ያጠቃበት ዕለት ስለሆነ በጣም ያማል ነው ያሉት።

ብዙ የካዱን ባዕዳን አሉ፤ የእነርሱን ቀናት አናከብርም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፥ ወገን፣ ዜጋ፣ ወዳጅ ምቹ ሁኔታን ጠብቆ አድብቶ የፈጸመው ጥቃት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መጥፎ ጠባሳ ስለሆነ እንዳይደገም ሁሌም እናስበዋለን ብለዋል።

ይህ ታሪክ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የማይጠፋ እና የሚመዘገብ አሳፋሪ ሁላችንንም አንገት የሚያስደፋ ታሪክ፤ ወንድም ወንድሙ ላይ የጨከነበት ቀን ነው ሲሉም አክለዋል።

እነዚህ ሰዎች መንግስት አዲስ ነው፣ ደካማ ነው፣ መሬት አልነካም፣ ሠራዊቱ እኛ የገነባነው ነው፣ የጎደለንን ትጥቅ ሰሜን ዕዝን በመምታት ካሟላን ማንም አያቆመንም ብለው ጦርነት እንደጀመሩም ጠቁመዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version