አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ደረጃ የማይመረቱ መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እና ለአፍሪካ የመድኃኒት ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል አለ የቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን።
ኢትዮጵያ መድኃኒትን በራስ አቅም ለማምረት እና አቅርቦትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ÷ ለዚህም በቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት እና ሕክምና አምራች ዘርፍ ማሕበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታደሰ ተፈሪ ለፋና ሚድያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት ÷ መድኃኒት፣ የመመርመሪያ እና የሕክምና ቁሳቁስ እንዲሁም የመድኃኒት ማሸጊያዎችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን ገበያ ውስጥ አስገብተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ግንባታ አጠናቀው ወደ ሥራ ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎች እንደሚገኙ ጠቁመው ÷ በርካታ የመድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች በግንባታ እና በዝግጅት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የተለያዩ መድኃኒቶች እና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ እየተመረተ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እየዋለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
መንግስት ዘርፉን ለማነቃቃት የሚያደርገው የፖሊሲ ማበረታቻ እጅግ ጠቃሚ እና መሰል እድል በበርካታ ሀገራት የማይገኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያነሱት ዶ/ር ታደሰ ÷ይህም ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ እንደሚያበረታታ አስረድተዋል።
የቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ምስክር ማሞ በበኩላቸው ÷ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ መድኃኒት እና መድኃኒት ነክ ምርቶች የሚመረቱበት እንደሆነ በመግለጽ ወደ 28 ከሚሆኑ አምራች ባለኃብቶች ውስጥ 5 የሚሆኑት በማምረት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሀገሪቱ የምትጠቀመውን የመድኃኒት ፍጆታ እና ፍላጎት መሰረት በማድረግ የማምረት ሥራው እንደሚከናወን ነው የገለጹት፡፡
በአፍሪካ ደረጃ የማይመረቱ መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እና ለአፍሪካ የመድኃኒት ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም አንስተዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ መድኃኒቶች የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚያስቀር እንደሆነ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒቶችን የሚገዛው የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎትም 65 በመቶ የሚሆነውን ግዢ በሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲያገኝ ማድረግ መቻሉን ነው ያስገነዘቡት፡፡
በዮናስ ጌትነት

