Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ፣ ፍጥነትና ጥራት መስራት ለሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ አስፈላጊ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ፣ ፍጥነትና ጥራት መስራት ለሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ አስፈላጊ ነው አሉ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

“በመደመር መንግሥት እይታ፣ የዘርፎች እምርታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቅቋል።

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ላይ የማጠቃለያ ስልጠና ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ፣ በፍጥነትና በጥራት መስራት ለሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ አስፈላጊ ነው።

በስልጠና መርሐ ግብሩ የመደመር መንግሥት ጽንሰ ሀሳብ፣ መንገድ እና መዳረሻ ግቦቹን በስፋት መዳሰሳቸው ተመላክቷል፡፡

በዚህም በመደመር መንግሥት መርሕ የሚመራው ፓርቲው አመራሮች በፈጠራና በፍጥነት በብዛት ሥራዎችን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል፡፡

የሕዝቡን ሁለንተናዊ ጥያቄ ከመመለስ በላይ የሀገሪቱን ራዕይ ለማሳካት እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚረዳ መንገድ መምራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት የሚሹ ግቦችን በየፈርጁ በመለየት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡

ፋይዳ፣ 5 ሚሊየን ኮደሮች፣ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች፣ የምርጫ ምቹነትና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም አጀንዳዎችን መቶ በመቶ ለማሳካት መትጋት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

መደመር ትውልድን ወደ ብልጽግና የሚያደርስ መንገድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ÷ የመደመር መንግሥት ለሀገር ብልጽግና ባለአደራ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በፈጠራና በፍጥነት ጥራትና ብዛትን እውን ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው ÷ በብዝሃ ዘርፍ ትስስር ወደ ስልጣኔ ሽግግር ማምጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የሀሳብ ሉዓላዊነት የብልጽግና መሰረት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ሁሉም የፓርቲው አመራር በዚህ አግባብ በመትጋት ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ አለበት ነው ያሉት፡፡

የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ባለፉት 11 ቀናት በስልጠና፣ በውይይትና በመስክ ጉብኝት እንዲሁም በማጠቃለያ ገለጻ ያገኟቸውን እውቀትና ልምዶች በዕቅድ በማካተት ወደ ሥራ እንዲቀይሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

Exit mobile version