አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ብሔራዊ መግባባትን የሚያመጣ ነው አሉ።
20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ‘ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት’ በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
የበዓሉን መሪ ቃል አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በተዘጋጀ የትንተና መድረክ ላይ አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ወንድማማችነትን አጠናክሮ ያስቀጥላል።
ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል እንደሆኑ አንስተው፤ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነዉ ሀገራቸውን ይገነባሉ ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዓሉ ሲከበር ብሔር ብሔረሰቦች ማንነታቸዉን እንዲገልፁ እና የሌላዉን ማንነት እንዲያዩ መደረጉን ተናግረዋል።
በዓሉ የሚከበርባቸው ክልሎች በበዓሉ ምክንያት ኢንቨስትመንትን እንዲያስፋፉ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጠርላቸውም አስረድተዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ለማጠናከር የሚመክሩበት መድረክ እንደሆነም አመልክተዋል።
20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ይከበራል።
በወንድማገኝ ጸጋዬ

