አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ ብልጽግና እንደምትራመድ የሰሜን ሸዋ ዞን ማሳያ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙትን የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርክ፣ የሴራሚክ ፋብሪካና የፐልፕ የወረቀት ፋብሪካዎችን ተመልክተዋል።
ፋብሪካዎቹ አዲስ ሀብትን ወደ ኢኮኖሚው የሚደምሩ መሆናቸውን ገልጸው፥ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተጀመረው ሀገራዊ የሪፎርም ትግበራ ውጤት ለማሳየቱ ምስክር ናቸው ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ዞኑ በኢንዱስትሪ ልማት ማበብ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ግዙፍ ተደማሪ አቅም ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በልዩ ትኩረት የያዘችው የአምራች ዘርፍ በባህሪው የሀብት ብዜትና የዘርፎችን ትስስር የሚፈጥር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በዚህም የአንዱ ምርት ለሌላው ግብአት እንደሚሆንና ዘርፉ በስራ እድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሪን በማዳን ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ሰላም እና ትጋት ሲኖር ፋብሪካዎች ለልማት፣ ዜጎች ለለውጥ ሀገርም ወደ ዘላቂ ብልጽግና እንደምትራመድ የሰሜን ሸዋ ዞን ማሳያ ነው ብለዋል።

