አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ኮፕ32ን እንድስታስተናግድ የተመረጠችው ተሰሚነቷ በመጨመሩ እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስኬቷ ነው አሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2027 የሚካሄደውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ “ኮፕ32” እንድታስተናግድ በብራዚል ቤለም በተካሄደው ኮፕ30 ላይ መመረጧ ይፋ ተደርጓል።
አቶ ከበደ ዴሲሳ ኢትዮጵያ መመረጧን አስመልክቶ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ መድረኮችን የማስተናገድ ዓቅሟ ጨምሯል።
ባለፈው ዓመት 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ እና የአፍሪካ ካረቢያን መሪዎች ጉባኤን ጨምሮ ከ150 በላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማስተናገዷን አስታውሰዋል።
ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች የሚታደሙበትን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ የተመረጠችው ብቁ ሆና በመገኘቷ እንደሆነም ተናግረዋል።
መሰረተ ልማትን ከማሟላት ባሻገር ሀገሪቱ የዲፕሎማሲያዊ አቅሟ መጠናከሩና ተደማጭነቷ መጨመሩ፣ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በብቃት ማስተናገዷ እና ተሳታፊዎች ደህንነታቸው መጠበቁ እንድትመረጥ ያደረጋት መሆኑን አብራርተዋል።
ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ የሰጠችው ትኩረትና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ያስመዘገበችው ስኬት እንዲሁም ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች እና ጫናዎችን ለመቋቋም የምታደርገው ጥረት ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ትኩረት ከለየቻቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እየሰራች መሆኗን ገልጸው፤ በተለይም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለያየ አጋጣሚ ኢትትዮጵያን እንዲጎበኝ የሚሰራው ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ ከሚደረግባቸው መንገዶች መካከል አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማስተናገድ እንደሚገኝበት ተናግረው፤ በዚህም ኢትዮጵያ የኮንፈረንስ ቱሪዝም አቅሟን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ማድረስ መቻሏን ጠቅሰዋል።
ጉባኤዎቹን በስኬት ማስተናገድ የተቻለው አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በተሰጠው ትኩረት እና በመጣው ውጤት መሆኑን ገልጸው፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የጉባኤ ተሳታፊዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ማዕከላትን መገንባትን ጨምሮ ሰፊ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
ለአብነትም አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ለተለያዩ ዓለምአቀፍ ስብሰባዎች ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶች ከስብሰባ ባሻገር በከተማዋ ተዘዋውረው የሚመለከቷቸው መዳረሻዎች መገንባታቸው እና የኮሪደር ልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ “ኮፕ32” እንድታስተናግድ መመረጧ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሟ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል ያሉት አቶ ከበደ፤ ባለፉት ዓመታት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማስተናገድ ያገኘችውን ልምድ በመጠቀም ጉባኤውን በስኬት ለማስተናገድ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።
በአቢይ ጌታሁን
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

