አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መፍጠር፣ መፍጠን እና በጥራት መሥራት የሁልጊዜም የሥራ መመሪያችን ሊሆን ይገባል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ በደብረ ብርሃን ከተማ በነበራቸው ቆይታ የመኪና መገጣጠሚያ እንዲሁም የብርጭቆና የጠርሙስ ማምረቻዎችን እንደተመለከቱ ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካዎች የሀገር ውስጥ ግብዓትን በመጠቀም እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን እያዳኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
ከብየዳ ጀምሮ ትላልቅ የኤሌትሪክ አውቶቡሶችን እየገጣጠመ የሚገኘው የፊቤላ ኢንዱስትሪያል መኪና መገጠሚያ በቀን 12 መኪና ማምረት የሚያስችል አቅም አለው ነው ያሉት፡፡
መገጣጠሚያው በቅርቡ ያስጀመረው አዲስ የቀለም መቀቢያ በርካታ ቀናትን ይወስዱ የነበሩ ሥራዎችን በሰዓታት ለማከናወን ማስቻሉን አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም በአንድ ቀን 450 ሺህ ጠርሙስ የሚያመርተውን ዴዴ ቦትል የብርጭቆና የጠርሙስ ማምረቻን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ 86 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት ከሀገር ውስጥ ተጠቅሞ ለበርካታ የመጠጥና የመድኃኒት ፋብሪካዎች ጥቅም የሚሰጡ ጠርሙሶች እንደሚያመርት ጠቁመዋል፡፡
የተመለከቷቸው አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴዎች በየዘርፉ በጥራትና በፍጥነት በመትጋት የታለመውን እድገት በአጭር ጊዜ ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል፡፡

