Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጉባዔን እንድታስተናግድ መመረጧ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ታሪካዊ ነው – መሐሙድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤዔን (ኮፕ 32) እንድታስተናግድ መመረጧ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ታሪካዊ ነው አሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ።

ሊቀመንበሩ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔን (ኮፕ32) እንድታስተናግድ በመመረጧ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጉባዔውን የማስተናገድ ውሳኔው ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ታሪካዊ መሆኑን ገልጸው ÷ ይህም አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ርምጃ ያላትን የማይናወጥ አቋም ያሳያል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት እያሳየች ያለውን የአየር ንብረት የመሪነት ሚናም ሊቀ መንበሩ አድንቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የደን መልሶ ልማትና አረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ ርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ ነው ያወሱት፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በስኬት በማስተናገድ እምቅ አቅም እንዳላት አንስተው ÷ከፍተኛ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉባዔዎችን ለማዘጋጀት ጠንካራ ተቋማዊ አቅምና ልምድ እንዳላት ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ጉባዔውን እንድታስተናግድ መመረጧ በዓለም አቀፍ ትብብር ያላትን ማዕከላዊ ሚና የበለጠ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ፣ ከተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ እና አጋሮች ጋር በመሆን (ኮፕ 32) ሁሉን አካታችና ውጤታማ በማድረግ የአፍሪካን የአየር ንብረት የቅድሚያ ትኩረቶች የበለጠ ለማራመድና ዓለም አቀፍ አጋርነት ለማጠናከር በቅርበት እንደሚሰራ ማረጋገጣቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version