አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን ድርቅን ለመቋቋም እና የዝናብ ስርጭትን ለመፍጠር ደመና የማበልጸግ ሥራ ጀመረች፡፡
ኢራን ባለፉት አስር ዓመታት የከፋ ድርቅን መጋፈጧ የተገለጸ ሲሆን ይህንን ችግር ለመፍታት እና የዝናብ ስርጭትን ለመፍጠር ደመና የማበልጸግ ሥራ ጀምራለች፡፡
ሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ደመና የማልጸግ ሥራ በኡርሚያ ሀይቅ ተፋሰስ ውስጥ ማካሄዷ ነው የተገለጸው፡፡
በሰሜን ምዕራብ የሚገኘው ኡርሚያ የኢራን ትልቁ ሐይቅ ሲሆን በድርቅ ምክንያት አብዛኛው የሐይቁ ስፍራ ወደ ሰፊ የጨው ቦታ መቀየሩ ተመላክቷል፡፡
በምስራቅ እና ምዕራብ አዘርባጃን ተጨማሪ ስራዎችን እንደምታከናውን የተገለጸ ሲሆን ባለፈው ዓመት ኢራን ለዚህ ዓላማ እና ዕቅድ የራሷን ቴክኖሎጂ ማዘጋጀቷ ተገልጿል፡፡
በትናንትናው ዕለት በምዕራብ ኢላም፣ ኬርማንሻህ፣ ኩርዲስታን እና ሎሬስታን እንዲሁም በሰሜንምዕራብ ምዕራብ አዘርባጃን ግዛት ዝናብ እንደጣለ ተዘግቧል።
በአብዛኛው በረሃማ የሆነችው ኢራን ለዓመታት ሥር የሰደደ ድርቅ እና የአየር ንብረት ለውጥ ሊያባብስ ይችላል ተብሎ በሚጠበቀው የሙቀት ማዕበል ለዓመታት መኖሯ ተገልጿል።
በቴህራን የጣለው ዝናብ በአንድ ምዕተ-ዓመት ውስጥ ዝቅተኛው ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት እንዳሉት፤ ከኢራን ግዛቶች ግማሽ ያህሉ በወራት ውስጥ የዝናብ ጠብታ እንዳላገኙ አስረድተዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ ሌሎች የቀጠናው ሀገራት ሰው ሰራሽ በሆነ መንገድ ዝናብ ለማግኘት ደመና የማበልጸግ ሥራን መጠቀማቸው ተመላክቷል፡፡

