አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 2ኛው የኢትዮጵያ እና ሳዑዲ ዓረቢያ የጋራ የንግድ ም/ቤት ስብሰባ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
መርሐ ግብሩ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
በመድረኩ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ፣ በሳዑዲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) እና በሳዑዲ የጋራ ም/ቤቱ ሰብሳቢ አብዱላህ አልአጂሚ የተመራ ልዑካን ቡድን አባላት ተሳትፈዋል፡፡
በስብሰባው በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማጠናከር እንዲሁም በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
አቶ ሰብስብ አባፊራ እንዳሉት÷ ምክር ቤቱ በሀገራቱ መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማስፋፋት እንዲሁም ጠንካራ የውይይት፣ የትብብርና አጋርነት መድረክ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
አምባሳደር ሙክታር (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ከኢኮኖሚ ሪፎርሙ ጋር ተያይዞ በርካታ የሳዑዲ ባለሃብቶችን ሊያሳትፉ የሚችሉ ዘርፎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
አብዱላህ አልአጂሚ በበኩላቸው÷ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ም/ቤት ሥራን የሚፈጥር፣ ዕድገትን የሚያነቃቃና የንግድ ፍሰቶችን የሚያጎለብት ነው ብለዋል፡፡
የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳለቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡
ከስብሰባው ጎን ለጎን የሳዑዲ ዓረቢያ ንግድ ማሕበረሰብ ልዑካን አባላት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
የኢትዮ ሳዑዲ ቢዝነስ ፎረም በነገው ዕለት ቀጥሎ እንደሚካሄድም ኤምባሲው ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

