አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ኢትዮጵያን አፍሪካዊ የዘላቂ ግብርና እድገት ማሳያ ለማድረግ እየተሰራ ነው አሉ።
የ2ኛው ምዕራፍ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን መርሐ ግብር ማስጀመሪያ መድረክ ላይ አቶ አዲሱ አረጋ እንዳሉት፤ ግብርናውን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት እያመጣ ነው።
ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ሽግግር ላይ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር፣ ፈጠራ የታከለበት እና አካታች ስራዎችን እየከወነች እንደሆነ ተናግረዋል።
የ2ኛው ምዕራፍ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን መርሐ ግብር 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ ይህም ኢትዮጵያ ለግብርናው ሽግግር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት።
አርሶ አደሩን ማብቃት፣ የገበያ ሰንሰለቱን ማጠናከር፣ በአነስተኛ እርሻ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ወደ ግብርና ንግድ ፈጠራ ማሸጋገርና ኢትዮጵያን አፍሪካዊ የዘላቂ ግብርና እድገት ማሳያ ማድረግ የመርሐ ግብሩ ግቦች መሆናቸውንም አስረድተዋል።
መርሐ ግብሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተመላክቷል።
በአሸናፊ ሽብሩ

