አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከማሌዥያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም ጋር ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ ባለፈው ዓመት በማሌዥያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከጉብኝታቸው አንድ ዓመት ቆይታ በኋላም የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂምን በኢትዮጵያ መቀበላቸውን ተናግረዋል፡፡
የጉብኝት ልውውጡ ጥልቅ አጋርነታችንን የሚመሰክር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም በርካታ ቁልፍ ሰነዶችን በመፈረም ተጠናክሯል ብለዋል።
የመግባቢያ ሰነዶቹ በቱሪዝም፣ ጤና፣ በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ በኳላ ላምፑር ከተማ ም/ቤት እና በአዲስ አበባ አስተዳደር የትብብር መስክ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በተካሄደው የሁለትዮሽ ውይይት ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር እና ለማስፋት ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት አረጋግጠናል ነው ያሉት።

