አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በ5 ሚሊየን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እስካሁን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎች ሥልጠናውን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት ወስደዋል አለ፡፡
በሚኒስቴሩ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስዩም መንገሻ እንዳሉት÷ ኢትዮ ኮደርስ ዜጎች ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ክህሎት እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡
ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው ያስገነዘቡት፡፡
የ5 ሚሊየን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መርሐ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በታቀደው መሰረት እየተከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
አሁን ላይ በመላ ሀገሪቱ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎች ሥልጠናውን በሚገባ አጠናቅቀው የምስክር ወረቀት ወስደዋል ነው ያሉት፡፡
ዜጎች በተለይም ወጣቶች የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ማሳለጥ የሚያስችለውን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

