Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ልማት የበኩሏን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ ናት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በመደመር ጽንሰ ሃሳብ በመመራት ለዓለም አቀፍ ልማት የበኩሏን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ ናት አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጆሃንስበርግ እየተካሄደ በሚገኘው የቡድን 20 የመሪዎች ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባዔው ባደረጉት ንግግር ÷ የጥንታዊ ሥልጣኔና ታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበች ነው ብለዋል፡፡

የመደመር ፍልስፍና ከኢትዮጵያዊያን የአይበገሬነት መንፈስ የሚቀዳ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በልዩነት ውስጥ አንድ በመሆን የተለያየ እምቅ አቅምን በማጣመር የተሻለ ነገርን ለመስራት ያለመ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዚህ ፍልስፍና በመመራት ኢትዮጵያ አካታች አድገትን እያስመዘገበች ትገኛለች ፤ ከተሞቿም የፈጠራ ማዕከል እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ኢኮኖሚውን በማነጽ ላይ የሚገኙ ሲሆን ÷ ወጣቶች አስደናቂ ፈጠራዎችን እውን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል እና በዲጂታል መሰረተ ልማት በርካታ ሥራዎችን በማከናወን የዜጎቿን ትስስር እያሳለጠች ትገኛለች ነው ያሉት፡፡

በግብርናው እና ሌሎች ዘርፎችም አመርቂ ሥራዎች እያከናወነች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ረገድ አበረታች ሥራ መከናወኑን አስታውሰው ÷ ለዚህም በአረንጓዴ ዐሻራ ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

በኃይል ልማት ዘርፍ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አካታች እና ቀጣይነት ያለው እድገት እውን ማድረግ ለአፍሪካ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል፡፡

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version