አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል የተከሰተው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ በንቁ ቅልጥ አለቶች መብላላት ምክንያት የተፈጠረ ነው አሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የሴስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አታላይ አየለ (ፕ/ር)፡፡
በአፋር ክልል ዛሬ ረፋድ 4 ሰዓት ላይ በኤርታአሌ ከወትሮው በተለየ መልኩ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተከሰተ ሲሆን፥ በአካባቢው ከፍተኛ የጭስ ደመና ፈጥሯል።
ኃላፊው ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ ከባድ የተባለው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተከሰተው በኤርታሌ ደቡባዊ ክፍል 10 ኪሎ ሜትር አቅራቢያ ሲሆን፥ ሁኔታውን ለማጥናት የጂኦ ፊዚክስ ተመራማሪዎች ወደ አካባቢው ተልከዋል፡፡
የዳናኪል ዝቅተኛ ስፍራ ንቁ የስምጥ ሸለቆ እየተካሄደበት የሚገኝ ስፍራ መሆኑን ገልጸው፥ የዛሬው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታም እንደ ወትሮው ሁሉ በንቁ አለቶች መብላላት የተከሰተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአካባቢው ቅልጥ አለቶች በየጊዜው እንደሚፈጠሩና በዚህም ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ እንደሚከሰት ተናግረዋል፡፡
ፍንዳታውን ተከትሎ ጠጠር እና ድንጋዮችን ወደ ሰማይ እንደሚወረወሩና ከፍተኛ ጭስ እና እሳት ነክ አመድ ሊያስከትል ይችላል ያሉት ኃላፊው፥ የአካባቢው ማህበረሰብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኤርታሌ እሳተ ገሞራ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ንቁ እሳተ ገሞራዎች አንዱ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ፍንዳታዎች መከሰታቸው ይታወሳል።
በሚኪያስ አየለ

